
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በአርባ ምንጭ ከተማ በማካሄድ በክልሉ መንግስት የ2018 የበጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡



መስተዳድር ምክር ቤቱ በዚሁ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ በተመለከተ አጀንዳው፡-
የበጀት ዕቅዱን በክልሉ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም፤ በሁሉም ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ እንዲሁም ክልላዊ የዘላቂ ሰላም፤ ልማትና የሁለንተናዊ ብልፅግና ራዕይን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ከማጠናከር አኳያ በመገምገም በዝርዝር ተወያይቷል፡፡



በዚህም ምክር ቤቱ የክልሉን መንግስት የ2018 ዓ/ም በጀት፡- የመደበኛ ወጪዎች፣ የካፒታል ወጪዎች፣ እንዲሁም ለዞኖች የሚሰጥ ድጎማን ጨምሮ በአጠቃላይ 53.2 ቢሊዮን (ሀምሳ ሶስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር) እንዲሆን በሙሉ ድምፅ በመወሰን ለክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት እንዲተላለፍ መርቷል።
ከበጀት አመቱ አጠቃላይ በጀት ውስጥ፡- ሃምሳ ሰባት ነጥብ ስድስት በመቶው (57.6%) በውስጥ ገቢ የሚሸፈን መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ቀሪው አርባ ሶስት ነጥብ አራት በመቶ (43.4%) በፌደራል መንግስት ድጎማ የሚሸፈን መሆኑም ተመላክቷል፡፡



ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት በክልሉ የውስጥ አቅምን በማጎልበት በራስ አቅም የህዝብ የልማትና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ መስራት በቀጣይም የክልሉ መንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በ2018 የበጀት ዓመት በክልሉ በሁሉም የአስተዳደር ዕርከኖች አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ እና በየደረጃው ለገቢ አሰባሰብ ስራ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን በተቀናጀ አግባብ በመሰብሰብ የውስጥ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


ክልሉ በርካታ ፀጋዎች አሉት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በየአካባቢው በግብርና፤ በኢንዱስትሪ፤ በቱሪዝም እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ያሉ እምቅ አቅሞችን ተጠቅሞ ከየዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በመስራት የገቢ ምንጮችን ማስፋት እንደሚገባም በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡
ምክር ቤቱ በተጨማሪም በክረምት በንቅናቄ የሚሰሩ ስራዎች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።