የክልሉ ሕዝብ ምክር ቤትና የብሔረሰቦች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘምን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በመካሄድ ላይ ይገኛል

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምክር ቤት እና የብሔረሰቦች ምክር ቤት 6ኛው ዙር 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በአርባ ምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በሥነ-ሥርዓቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን እንደጀመሩ በማብሰር የክልሉን መንግስት የ2018 የልማት ዕቅድ በዋና ዋና የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ በማተኮር የሚያቀርቡና የትኩረት አቅጣጫዎችንም የሚያስቀምጡ ይሆናል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ የመክፈቻ ንግግራቸው፤ የክልሉ መንግስት በ2018 ለክልሉ ሕዝብ አዳሪና አዳጊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ብቃት ያለው ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ለክልላዊ የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ራዕይ ስኬት አቅም መፍጠር የሚያስችሉ የልማት ዕቅዶችን ይዳስሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

በተለይ በዋና ዋና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዘርፎች የክልሉን ህዝቦች አብሮ የማደግና የመልማት ትልም  ማዕከል ያደረጉ፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመደረግ ላይ ያለው ሽግግርን ይበልጥ የሚያጎለብቱ እና ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የብልጽግና ግብ ስኬት የላቀ ሚና ያላቸው የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱም ይሆናል፡፡   

የክልሉ መንግስት በ2017 በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በሁሉም የልማት አውታሮች ዘርፍ ብዙ ውጤታማ የሰላም፤ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በመስራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ይታወቃል፡፡

በ2018 የበጀት አመትም ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሰረት በየዘርፉ የተጀመሩ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ ከዳር በማድረስ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ርብርብ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በምክር ቤቶቹ የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply