ለከተሞች ቀጣይነት ያለው ዕድገት ዘመናዊ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፤ ጠንካራ ገቢ እና ንቁ የህብረተሰብ ተሳትፎን ማዕከል በማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከርና ማስፋት ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የቦዲቲ ከተማን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታላይዝ በማድረግ ማዘመን የሚያስችል የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ በይፋ አስጀምረዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደ ሀገር ባለፉት የለውጥ አመታት ለከተሞች ዕድገትና ልማት በተሰጠው ልዩ ትኩረት፤ በሀገራችን የከተሞች ዕድገት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ በመክፈት አስደናቂ ዕድገት በመመዝገብ ላይ የሚገኝ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የስልጡና ማህበረሰብ መለያው ዘመናዊነት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አሁን ላይ በክልሉ ከተሞችን የማዘመን ስራ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

ማዘጋጃ ቤት ስሙ በአሉታዊ መንገድ የሚነሳ፤ ብዙ እሮሮዎችን የሚያስተናግድ፣ የመሬት ደላላ ዜጎችን የሚያማርርበት መሆኑን ገልፀው፤ አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመኑ በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን የሚረዳ መሆኑን ተናግረውል።

የክልሉ መንግስት ከተሞችን በዕቅድና በፕላን የሚመሩ፤ ለኑሮ ምቹ፤ ለኢንቨስትመንት ተመራጭና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ባለፉ ጊዜያት በተከናወኑ በርካታ ስራዎች የክልሉን ከተሞች በፈጣን የለውጥ ሂደት ላይ እንዲገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን ዘመኑን በዋጀ፤ በቴክኖሎጂ በተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመኑ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የተገልጋዩን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ለአገልጋዩ ምቹ  አካባቢን  ለመፍጠር የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ለከተሞች ዕድገት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘመናዊ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ የከተሞች ተወዳዳሪነት እና ተመራጭነትን በማስፋት፤ ቀጣይነት ያለው የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ለከተሞች ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ልማት ዘመናዊ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፤ ጠንካራ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ እና ንቁ የህብረተሰብ ተሳትፎ ቁልፍ ስለሆኑ በዚህ ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከርና ማስፋት እንደሚገባ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም አመራሩ እና ህብረተሰቡ በከተሞች የተቀላጠፈ ዘመናዊ አሰራር ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም በማዘጋጃ ቤታዊ የገቢ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ውስንነቶችን በመቅረፍ የውስጥ ገቢን አሳድጎ በአግባቡ ለልማት ማዋል እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ በማድረግ ማዘመኑ የተገልጋዩን ህብረተሰብ ዕርካታ የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ከተማን በተጠናና በታቀደ መልኩ በማስተዳደር ለታለሙ የከተሞች ዕድገት ግብ ስኬት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

አገልግሎት ማዘመኑ የማዘጋጃ ቤት የብዙ እሮሮ ማዕከል መሆኑን በማስቀረት፤ የህብረተሰቡን እርካታ የሚጨምርና ህዝቡን ከመንግስት ጋር የሚያቀራርብ መሆኑንም ጨምረው  አስገንዝበዋል።  

Leave a Reply