
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን የአረካ ከተማን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታላይዝ በማድረግ ማዘመን የሚያስችል የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ በከተማው ማዘጋጃ ቤት በመገኘት በይፋ አስጀምረዋል፡፡


በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አረካ ብዙ ፀጋዎች ያሏት በየጊዜው ለውጥ እያሳየች የምትገኝ ከተማ መሆኗን ገልፀው፥ ለስኬቱ የከተማዋን አመራሮች አመስግነዋል።



በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ በየምዕራፉ በጥሩ መልክ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰው፥ ከተማዋን ውብ፥ ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመረው ስራ የሚበረታታ እና ተጠናክሮ ልቀጥል የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።


በተቀላጠፈ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ የከተሞች ዕድገትን ማሳለጥ በከተሞች ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ባሻገር የክልሉን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያፋጥን መሆኑንም ገልጸዋል።
ዘመናዊ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ የከተሞች ተወዳዳሪነት እና ተመራጭነትን በማስፋት፤ ቀጣይነት ያለው የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡


ከተማ ለመቀየር ወሳኙ የከተማዋ ነዋሪ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለከተሞች ቀጣይነት ያለው ልማት ግንባር ቀደም የህብረተሰብ ተሳትፎ እና ጠንካራ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
መሠረተ ልማት የተሟላላቸው፤ የለሙና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ስማርት ከተሞችን ለመፍጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ርብርብ አስፈላጊ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ በአጽንኦት ገልጸዋል።


በክልሉ የተማሏ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎት በመዘርጋት ስማርት ከተሞችን ለመገንባት ለተያዘው ውጥን የተጀመሩ ስራዎችን ያደነቁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም ወደ ሌሎች ከተሞች በማስፋትና በማዘመን ከተሞች የብልጽግና ማዕከላት እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውደ በበኩላቸው፥ አረካ ከተማ ከነበረበችበት የፈርጅ ሁለት ወደ ፈርጅ አንድ መሸጋገሪያ የዕውቅና መርሃ ግብር እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
ከተሞች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለውጥ እያሳዩ መምጣታቸውንም ተናግረው፥ የከተሞች ፈርጅ ለውጥ ለከተሞች እድገትና ለአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።