
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከህዳር 20 እስከ የካቲት 30 በሚፈጸሙ በቀጣይ የ 100 ቀናት ስራዎች ዕቅድ ዙሪያ በየደረጃው ካሉ የክልል፤ የዞንና የረጂዮ ፖሊስ ከተሞች አስፈጻሚ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በበይነ መረብ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እምርታ በሚል መሪ ሃሳብ በሁለት ዙር ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሩ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰው፤ ስልጠናው የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም የገነባ ከመሆኑም በላይ ሀገራዊ አቅሞችን ገልጦ ማሳየት የቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


በስልጠናው በክብር ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በየዘርፉ እምርታ በማስመዝገብ እንደ ሀገር በወጥነት ልናሳካ የሚገቡ ሀገራዊ ግቦች መቀመጣቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የተቀመጡ ግቦችንና የተመላከቱ ቀጣይ አቅጣጫዎች በብቃት በመምራት ለውጤት ለማብቃት የ100 ቀን እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባት ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህም በክልሉ በየደረጃው የሚገኘው አመራር በሁሉም መዋቅሮች መፍጠር፤ መፍጠንና መዝለል የመደመር መንግስት መርሆች፤ መርህ በማድረግ የታለሙ ስራዎችን ከተለምዷዊ አሰራሮች ወጣ ባለ መልኩ በመስራትና በመፈጸም በስልጠናው ያዳበረውን አቅም ወደ ውጤት መቀየር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የ መቶ ቀን ዕቅዱ ሲዘጋጅ በንቅናቄና በመደበኛ የሚመሩና የሚሰሩ ስራዎችን በመለየት ስልጠናው በአመራሩ ላይ የፈጠረው ውጤት፣ ከስልጠናው ማግስት የዘርፎች እምርታ ለማስመዝገብ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እንዲሁም ያሉ ተጨባጭ አቅሞችን ተጠቅሞ ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት አግባብ በመፈጸም ለውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ ስልቶችን ታሳቢ ያደረገ ልሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡



የክልሉ መንግስት የስራዎችን ስኬት የሚከታተል ግበረ ሀይልና የድጋፍና የሱፐርቪዠን ቡድን በማቋቋም በየደረጃው ባሉ አስፈጻሚ ተቋማት ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን ጨምሮ ህዝበዊ ውይይቶች በማድረግ ስራዎች ህብረተሰቡን ባለቤት ባደረገ መልኩ እንዲመሩ የሚሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በየደረጃው ሊገጥሙ የሚችሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እንዲሁም በየዘርፉ የሚከናወኑ ስራዎች ውጤታማነት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በመደመር መንግስት ዕይታ በየዘርፉ እምርታዊ ለወጥ በማስመዝገብ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የሚያስችሉ ስራዎችን እንችላለን የሚል እሳቤን ተላብሶ በመሉ አቅም በከፍተኛ ኃላፊነትና የባለቤትነት ስሜት መምራትና መስራት እንዲምገባም አሳስበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ 100 ቀናት መቶ በመቶ ሊሳኩ የሚገቡ እና በእጥፍ ለማሳደግ መሰራት ያለባቸው ተግባራትን በመለየት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችንም አስቀምጠዋል፡-
* ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ የሆኑ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እና የ 5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ግቦች ሙሉ በሙሉ ለማሳካት በልዩ ትኩረት መስራት፤
* የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ስራዎችን በተቀመጠው የግዜ ሰሌዳ አጠናቆ ተግባራዊ በማድረግ የታለመውን ውጤት ማምጣት፤
* መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ በሁሉም የከተማ አስተዳደሮች እንደከተሞች ነባራዊ ሁኔታ በማስፋት በክልሉ የአገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፤ ፈጣንና ቀልጣፋ የማድረግ፤ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከዳር የማድረስ እንዲሁም ከተሞችን ስማርት የማድረግ ተግባራትን ማጠናከር፤
* የገቢ አሰባሰብ ስራዎችን በልዩ ትኩረት በቅንጅት በመምራት በተለይም መደበኛና የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ እና የአርሶ አደር ገቢ ግብር በአግባቡ በመሰብሰብ እንዲሁም አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ በሁሉም አካባቢ ተግባራዊ በማድረግ ከተጣለው ግብ በላይ ማሳካት፣
* የገጠር ኮሪደር ልማትን በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች በመጀመር የታለመውን የገጠር ሽግግር ለማሳካት፤ የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻልና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት፤
* በቱሪዝም ዘርፍ የክልሉን እምቅ አቅም መጠቀም በሚያስችል አግባብ በሁሉም ዞን እና ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ማዕከላትን መለየት፤ ማልማትና የቱሪዝም ኢንፎርሜሽን ማዕከላትን ስራ በማስጀመር ማስተዋወቅ፤
* በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ኢንዱስትሪን በእጥፍ የማሳደግና የማስፋት ተግባራትን ማጠናከር እንዲሁም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ለመጀመር የሚስችል የቦታ ዝግጅት የማድረግ ስራዎችን መስራት፤
* በግብርና ልማት ዘርፍ ግብርናን የማዘመን ተግባራትን የማጠናከር፤ የበጋ መስኖ ልማትና የበልግ እርሻ ስራዎችን በትኩረት በመከወን ምርታማነትን የማሳደግ፤ በአርብቶ አደር አከባቢዎች የእንስሳት ጤና ማዕከላትን የማስፋት እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ስራዎችን በማስፋት የእንስሳት ሀብት ልማት ምርታማነትን ማሳደግ፣
*በጤናው ዘርፍ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን የመከላከልና ስርጭቱን የመቆጣጠር ውጤታማ ተግባራትን በማጠናከር ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ መስራት፤
በተጨማሪም በተለያየ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ የተፈናቀሉ ዘጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስና በዘላቂነት የማቋቋም ተግባራትን ከዳር በማድረስ የተረጂነት ቁጥርን ዜሮ ማድረግ፤ የኑሮ ውድነት ጫናን የመቀነስና ገበያ የማረጋጋት ተግባራት እንዲሁም የክልሉን ሰላም የማፅናት የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን የማጠናከር ስራዎች የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ አካል መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡




