
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በቪታ (vita) መንግስታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆን ዊሊያም የተመራ ልዑክ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አናጋግረዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ መንግስት ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬትና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በተለያዩ የልማት ትብብሮች ከተለያዩ አጋር ሀገራት እና ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ላይ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህ ረገድ ቪታ በአይርላንድ መንግስት ድጋፍ ለረዥም ግዜያት በኢትዮጵያ የተለያዩ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ የማሻሻል አላማን አንግቦ በርካታ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።


ድርጅቱ በተለይም ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት በመስራት የገጠሩን ህብረተሰብ ኑሮ ለማሻሻል የሚያግዙ የተለያዩ ውጤታማ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ድርጅቱ ያቀደው የአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት አካል የሆነው አዲሱ የማህበረሰብ ደን ልማት ፕሮግራም፤ መንግስት በከፍተኛ ትኩረት በመስራት ላይ የሚገኘውን የግሪን ሌጋሲና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።



ከዚህም ባለፈ ቪታ የሚያከናውናቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሩ ሁኔታ ለማሻሻል ያለሙ ፕሮጀክቶች፤ መንግስት ሰው ተኮር ለሆኑ ተግባራት ልዩ ትኩረት በመስጠት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በማድረግ ላይ ላሉ ጥረቶች ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በተለይ መንግስት የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል የገጠር ሽግግርን ለማረጋገጥ አቅዶ በመስራት ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፤ ድርጅቱ የገጠሩን የህብረተሰብ ክፍል በተለይም የሴቶች የኑሮ ጫና በሚያቃልሉና በማህበረሰብ ተኮር የአረንጓዴ ልማት ስራዎች መሰማራቱ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ እንደ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ጠንካራ ስትራቴጅክ አጋር ከመንግስት ጋር በቅርበት በመስራት ልማቱን እያገዘ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የድርጅቱ የረዥም ግዜ የልማት አጋርነት ዕውቅና የሚሰጠው መሆኑን ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ድርጅቱ በክልሉ የገጠሩን የህብረተሰብ ክፍል የኑሮ ሁኔታ የማሻሻል፤ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ተደራሽ የማድረግ እንዲሁም ማህበረሰብ አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁ ሲሆን፤ የክልሉ መንግስት ለድርጅቱ ስራ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆን ዊሊያም በበኩላቸው፤ የአይርላንድ ህዝብና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የረዥም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዘላቂ ልማትና በግሪን ለጋሲ ጨምሮ በሁሉም ረገድ አስደናቂ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ መሆኗን ገልፀዋል፡፡
አክለው ቪታ ከዚህ ቀደም በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፤ አዲስ የተጀመረው ፕሮግራም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ከባቢና ማህበረሰብ መፍጠር ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በጋሞ ዞን የተለያዩ ገጠራማ አካባቢዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ፤ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ተደራሽ የማድረግ፤ የህብረተሰቡን ኑሮ የማሻሻል እና ተያያዥ ተግባራት ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል።
በቀጣይም ድርጅቱ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ህብረተሰብ ለመፍጠር ያለመ፤ ከ2025 -2029 ድረስ የሚቆይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ፣ ወላይታ፤ ጎፋ፤ ኮንሶ እና ጋርዱላ ዞኖች የማህበረሰበብ ደን ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ በአዲስ መልክ ስራ የሚጀምር መሆኑን አስታውቀዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ድርጅቱ መንግስት የሚያከናውነው የግሪን ለጋሲ ተግባር የሚደግፍ መሆኑንም ገልፀው፤ ለዚህም ችግኝ በመትከል ፣ በመንከባከብና ጊዜውን ጠብቆ ለካርበን ሽያጭ በማዋል ህብረተሰቡን በተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።




