
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮምሽን ኮምሽነር ብርሃኑ አዴሎ የተመራ ልዑክ ጋር በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅና አያያዝ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮምሽን የዜጎችን የሰበአዊ መብቶች መጠበቅ በመከታተልና በማረጋገጥ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።


ኮሚሽኑ የለውጡ መንግስት ያነገበውን የራስን ችግር በራስ አቅም የመፍታት መርህ በተግባር እያሳካ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት በመንግስት ስራዎች የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት ለማረም እና በጋራ ተናቦ ለመስራት እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ በክልሉ ህዝቦች ነፃ ፍቃድና ይሁንታ ፍጹም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ የተመሰረተ ቀዳሚ የብዝኃ ህዝቦች መገኛ መሆኑንም ገልጸው፤ በክልሉ ካሉ ብዝኃ ባህል፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት እና ሌሎችም ብዝኃ ማንነቶች አንፃር ሰላምና መቻቻልን ዋና መርህ አድርጎ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


የክልሉ መንግስት ለዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ቁርጠኛ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም ህጋዊና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መሠረት በማድረግ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ እና ለዜጎች ሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ መከበር አበክሮ በመስራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምንጭ የሆኑ አላስፈላጊ ግጭቶችን ከምንጫቸው ለማድረቅ በክልሉ የሰላምና የመቻቻል እሴቶችን እና ችግሮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህል ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትን በትኩረት በማከናወን ውጤታማ ስራ መስራት መቻሉን ተናግረዋል፡፡


የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት ከትላንት በመማር ትክክለኛ የሰብአዊ መብት ጥበቃን ለማስረፅ እየተሰራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም በክልሉ ያሉ ባህላዊ የዳኝነት እሴቶችን፤ የሀይማኖትና የሀገር ሽማግሌዎች ፎረም በማቋቋም እንዲሁም የሽግግር ፍትህ ስራዎችን በመስራት የተገኙ ውጤቶች ይጠናከራሉ ብለዋል።
በክልሉ ምስረት ማግስት ለነበሩ የአደረጃጀት ጥያቄዎችና ላደሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ብቃት ያለው ምላሽ በመስጠት ወደ ስራ መገባቱንም አውስተው፤ አሁን ላይ በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በሙሉ አቅም ወደ ልማት መገባቱን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችንም ሆነ አዳጊ የህዝብ ጥያቄዎችን በመፍታቱ ረገድ በትብብር የመስራት ልምድን በማዳበር በህጋዊ መንገድ ከሚንቀሳቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት በማቋቋም ጭምር በጋራ በመሰራት ላይ መሆኑንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡


የክልሉን ሰላም በማደፍረስ ቀጠናውን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ በህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ የጥፋት ሃይሎች መኖራቸውንም ጠቅሰው፣ የክልሉ መንግስት ዜጎችን ከነዚህ ሃይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴና እኩይ ተግባር በመጠበቅ ሰብአዊ መብታቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በሕገ-መንግስት የተቋቋመ ነፃና ገለልተኛ ለህዝብ የቆመ ተቋም መሆኑን ተናግረው፤ ለዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ክልሉ ከሰብአዊ መብቶች አያያዝ አኳያ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ኮምሽነሩ፤ በተለይ ከታራሚዎች አያያዝ፣ ለተፈናቃዮች የሚደረገ ድጋፍና ክትትል በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኮምሽነሩ በክልሉ ግጭት በመፍጠር ዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ይበልጥ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይም የሽግግር ፍትህ ተግባራት የማፋጠን፤ ከኮምሽኑ ጋር የመረጃ ልውውጥ የማጠናከር እንዲሁም እኩይ ተግባር በሚፈፅሙ አካላት የሚያደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የመከላከል ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።