ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ህብረት የሰላም ሜዳልያ እና ልዩ ዕውቅና ተሰጣቸው       

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት 5ኛው ሀገር አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ የሰላም፤ የመቻቻልና የብዝኃነት ተምሳሌት በሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በሰላም ሰገነቷ በውብቷ አርባ ምንጭ ከተማ በታላቅ ህዝባዊ ተሳትፎ በድምቀት ተካሂዷል፡፡

”ኃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለአብሮነት” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው ጉባኤው፤ የኃይማኖት ተቋማት ለሰላም፣ ለመከባበርና ለአብሮነት ያላቸውን ሚና ያጠናከሩበት ከመሆኑም በላይ ሀገር አቀፍ የሰላም እሴቶችን በማጎልበቱ ረገድ ከፍተኛ አስትዋጽኦ ያበረከተ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ 

በጉባኤው ማጠቃለያ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ህብረት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ለሰላም ላበረከቱት አስትዋጽኦ እንዲሁም ጉባኤው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እጅግ በደመቀና ባመረ መልኩ በሰላምና በስኬት እንዲካሄድ ላደረጉት አበርክቶ ልዩ የሰላም ሜዳልያ እና ዕውቅና ተበርክቶላቸዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የሁሉም ነገር መሠረት ለሆነው ሰላም ሁሌም ቅድሚያ መስጠት በሚል መርሃቸው የሚታወቁ ሲሆን፤ በተለይ ክልሉን የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ በመሰነቅ በክልሉ ህዝብ ባለቤትነት ሰላምና ፀጥታው የተረጋገጠ፤ ቀዳሚ የብዝኃ ሕዝቦች የጋራ ቤት ማድረግ ችለዋል፡፡

በተለይ ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ለሰላም በሰጡት ልዩ ትኩረት፤ የክልሉ መንግስት ከክልሉ ምስረታ ማግስት ጀምሮ “ሰላምን በሰላሙ ጊዜ!” በሚል ዕሳቤ የልማት የደምስር ለሆነው ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ የክልሉን ህዝቦች ድንቅ የሰላም እሴቶች እና ማህበራዊ ተቋማት በመጠቀም ጭምር ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ የሰላም ግንባታ ስራዎች ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ማድረግ ችሏል፡፡

ከዚህም ባለፈ በክልሉ ሰላምን በማስቀደም በሰላምና በልማት አርበኛው የክልሉ ህዝብ ንቁ ተሳትፎ የማይቻሉ የሚመሰሉ አስደማሚ ስኬቶች ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን፤ የተመዘገቡ ውጤቶች አንድነታችን ኃይላችን፤ መተባበራችን መቻላችን፤ ሰላማችንም የልማታችን መሠረት መሆኑን በተግባር አሳይተውናል፡፡   

የምንሻው ዕድገት፤ ዘላቂ ልማት እና የተሻለ ነገ በፈተናዎች በመፅናት ሰላምን አስቀድሞ፤ የጥላችን ዛር በመንቀል እና የተረጂነትና የጠባቂነት ቀንበርን በመስበር በራስ አቅም መቻልን ተላብሶ በመደመር መንገድ እጅ ለእጅ ተያይዞ በኅብረትና በትብብር መትጋትን ይጠይቃል፡፡

ጉባኤው ሀገርን የሚያሻግሩ የሰላም፣ የብዝኃነት፣ የመቻቻል፣ የአብሮነትና የኅብረ-ብሔራዊነት እሴቶች፣ ቱባ ባህሎችና ሥርዓቶች መገኛ በሆነው ክልላችን መካሄዱ፤ በክልሉ ያሉ የሀገርን ሰላም ለማፅናት የሚያስችሉ የዳበሩ ተሞክሮዎችን ለማካፈል ዕድል የፈጠረ ሆኖ አልፏል፡፡

በጉባኤው ማጠናቀቂያ ለጉባኤው መሳካት የላቀ አስትዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን፤ ቀጣይ የጉባኤው አዘጋጅ ጋንቤላ ክልል መሆኑን በማሳወቅም የሰላም ዋንጫውን ለክልሉ በማስረከብ ጉባኤው በስኬት ተጠናቋል።

በጉባኤው ከክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ህብረት የበላይ አካላት፤ የኃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና ከሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ የመጡ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡   

Leave a Reply