ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን አረካ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጨምሮ በከተማው አቅራቢያ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የሱማሞ አየር ማረፊያ የግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ የአረካ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡን አስተባብሮ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎች የሚበረታታ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጀማሪነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ በክልሉ ተግባራዊ ሆኖ ተጨባጭ ውጤት እየመጣ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በመርሃ ግቡሩ በከተማው የተጀመሩ ስራዎች ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በእንስሳት ሃብት ልማት ያለን አቅም ተጠቅሞ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባለፈ:-
በከተማ እና ገጠር ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ፥ ለስርዓተ ምግብ መሻሻል፥ ገበያ ለማረጋጋት እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ በመሆኑ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
የአረካ ከተማ የኮሪዶር ልማት ስራ በተመለከተም በከተማው ነዋሪዎች ንቁ ተሳትፎ በመከናወን ላይ የሚገኘው የኮርደሪ ልማት ያደነቁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ይህንን ማስፋትና ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአረካ ከተማ አቅራቢያ እየተገነባ ያለው አየር ማረፊያ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ቀንና ማታ መስራት እና ግንባታውን ማፋጠን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የክልሉ መንግስት በአየር ማረፍያው የግንባታ ሂደት ላይ መስተጓጎል እንዳይኖር እና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የአየር ማረፍያው በዲዛይኑ መሠረት መሰራት እንዳለበት ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ፕሮጀክቱ ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ፈጥኖ መጠናቀቅ ይኖርበታል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንደ ክልል “ከተረጂነት ለመላቀቅ” በመደረግ ላይ ባለው ጥረት አርሶ አደሩ እየሰራ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪ እንደሆነም በጉብኝቱ ወቅት አንስተዋል።
በዚህ ረገድ በወላይታ ዞን ባህር ዛፍን ከማሳ በመንቀል በሰብል የመተካት ስራ የሚበረታታ እንደሆነ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ይህም በኢኮኖሚ አዋጪ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጴጥሮስ ወ/ማርያም በበከላቸው፥ በዞኑ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በከተሞች የተጀመሩ የኮርደሪ ልማት ስራዎች ለከተሞች ውበት ከመስጠት ባለፈ ለወጣቶች ስራ ዕድል እየፈጠሩ በመሆኑ በሁሉም አከባቢዎች ማስፋትን ይጠይቃል ብለዋል።
በዞኑ የሌማት ትሩፋትን በመንደር በማደራጀት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፥ በጉብኝቱ በአረካ ከተማ የታየው ከዚህ አንዱ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የአየር ማረፊያ ግንባታው በተቀመጠው ጊዜ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ የዞኑ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

