ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን የሱማሞ አየር ማረፊያ የግንባታ ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ ምልከታ አደረጉ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን አረካ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጨምሮ በከተማው አቅራቢያ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የሱማሞ አየር ማረፊያ የግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ ምልከታ አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመስክ ምልከታቸው ወቅት በግንባታው ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በመገምገም ስራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ መሰራት ባለባቸው ስራዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመስክ ምልከታው ከዚህ ቀደም የአየር ማረፊያው ግንባታ እንዳይጀመር ማነቆ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ርቀት መከዱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የነበሩ ማነቆዎች ተፈተው ስራው መጀመሩ አበረታች መሆኑን ገልፀዋል።

መጪው የበልግ ዝናብ ወቅት ከመሆኑ አንፃር ግንባታውን እንዳያስተጓጉል አሁን ላይ ማለቅ ያለባቸው ስራዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኤርፖርት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ ለክልሉም ሆነ ለቀጠናው የጎላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም የክልሉ መንግስት በግንባታው ሂደት መስተጓጎል እንዳይኖር እንዲሁም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችንም በቅንጅት ለመፍታት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

በመስክ ምልከታው ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የክልሉ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተን ጨምር የወላይታ ዞን አስተባባሪ አካላት ተገኝተዋል።

Leave a Reply