
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ በጌዴኦ ዞን፤ ራጴ ወረዳ በጫራቃ እና በሀሮ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በስፍራው በመገኘት አፅናንተዋል።
በአካባቢው ለሁለት ተከታታይ ቀናት የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ፤ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።


ርዕሰ መስተዳድሩ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝተው በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች በማጽናናት በተከሰተው ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ በጠፋው የውድ ወገኖቻችን ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል።
የክልሉ መንግስት ከዞኑ አስተዳደር ጋር በቅንጅት በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግና በአካባቢው አፋጣኝ የአደጋ ምላሽ ከመስጠት ባላፈ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በአካባቢው እየጣለ ካለው ዝናብ ጋር ተያይዞ መሰል አደጋዎች ተከስተው ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ የተጀመሩ የቅድመ መከላከል ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከወትሮ መጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ በመጣሉ በሌሎች አካባቢዎችም መሰል አደጋዎች የተከሰቱና በቀጣይም ሊከሰቱ የሚችሉ በመሆኑ፤ ለናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡
በተለይ የአደጋ ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች በየደረጃው ያለው አመራር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሲከናወኑ የቆዩ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡



በአደጋው ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች የማስጠለል እንዲሁም በአካባቢው ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ስፍራዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ደህንነቱ ወደ ተረጋገጠ ቦታ የማሻገር ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፤ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ስራዎች በመሰራት ላይም ይገኛል፡፡



ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም በስፍራው ተገኝተው በአደጋው ምክንያት ባለፈው የዜጎች ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ፤ በአደጋው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሁሉ መፅናናትን ተመኝተዋል።