
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለይፋዊ የስራ ጉዳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወደ ጎፋ ዞን በማቅናት በሳውላ ማዕከል የስራ ቆይታ አድርገዋል፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ ለይፋዊ የስራው ጉዳይ ሳውላ ከተማ ስድርሱ በክልሉ የሳውላ ማዕከል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ በጎፋ ዞንና በሳውላ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም በሀገር ሽማግሌዎችና በከተማዋ ነዋሪዎች እጅግ ደማቅ የሆነ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ በዞኑ በነበራቸው የስራ ቆይታ በተለይ በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ተከስቶ በነበረው አስከፊው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራው አካል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያስገነባቸው ቤቶችን ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል፡፡
በአካባቢው ተከስቶ የነበረው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ፤ የበርካታ ወገኖች ህይወት መቅጠፉ እና ከ600 በላይ አባወራዎችን ማፈናቀሉ ይታወሳል፡፡


የክልሉ መንግስት አደጋውን ተከትሎ ከፌዴራል መንግስት፤ ከዞኑ አስተዳደር እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ ተቋማትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማቋቋም እና የአደጋ ስጋት ያለባቸውን ከአደጋ ስጋት ነፃ የማድረግ ውጤታማ ስራ አፅኖት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል።