
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በወላይታ ዞን፥ ዳሞት ፑላሳ ወረዳ በሻንቶ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት መርቀው በይፋ አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡



ከ 208 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከ 30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የሻንቶ ከተማና ለአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑ ተገልጿል።



ፕሮጀክቱ ከ26 ኪሎ ሜትር በላይ የግፊትና የስርጭት መስመሮችን የሚሸፍን ሲሆን፥ ዘመናዊ የሳኒቴሽን አገልግሎት ሰጪ ክፍሎችን ያካተቴ መሆኑም ታውቋል።



በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በአካባቢው የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ለዘመናት የህዝብ መሠረታዊ ጥያቄ እንደነበር ጠቅሰው፥ ፕሮጀክቱ ለዚህ የህዝብ ጥያቄ ምላሽ በሚሰጥ አግባብ በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።



ፕሮጀክቱ ጊዜ የወሰደ ቢሆንም የለውጡ መንግስት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየሰራ ባለው ብርቱ ስራ፥ ችግሮች ተፈተው የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቱ ከተማውን ከፍ በሚያደርግ መልኩ ለመጠናቀቅ የበቃ የክልሉ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።



በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን የመጠጥ የውሃ ፕሮጀክት ጠብቆ ተንከባክቦ በማቆየት ህብረተሰቡን በአግባቡ ማገልገል እንዲችል መስራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።







በአካባቢው ውሃ እንደ ልብ ማግኘት እንዲቻል ህብረተሰቡ አካባቢውን በመንከባከብ፥ ችግኝ በመትከል ጠብቆ ማቆየት ይገባዋል ሲሉም አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ውሃ ህይወት መሆኑን ተረድተን የውሃ ታሪፍን በማሻሻል ዘለቄታዊ የውሃ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በመጨረሻም ርዕሰ መስተዳድሩ ለኢፌድሪ ውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እና ሌሎች ለፕሮጀክቱ ስኬት አስትዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚንስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በቡካላቸው፥ ሚንስተር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በክልሉ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ዞኖች ላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከንፁህ መጠጥ ውሃ ባሻገር ከተሞች ንፅሁና ጥራት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራም በትኩረት እንደሚከናወን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ የውሃና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በበኩላቸው፥ የክልሉ መንግስት በጀት በመመደብ እና ሌሎች የበጀት አመራጮችን በመጠቀም በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ገልፀዋል።
በሻንቶ ከተማ የተመረቀው የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የዚሁ አካል መሆኑን ክቡር ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።





በተጨማሪም ርዕሰ መስተዳድሩ እና ክቡር ሚኒስትሩ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አካል በሻንቶ ከተማ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።
በመርሃ ግብሩ ከርዕሰ መስተዳድሩ እና ከክቡር ሚኒስትሩ በተጨማሪ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።