ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የአንጋፋው አርቲስት ፊሻሌ ሚልካኖ እና የሁለት የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ በማስጀመር ክልላዊ የአንድ ጀንበር ቤት ግንባታ ስራን በይፋ አስጀመሩ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በመከናወን ላይ የሚገኘው የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የአንድ ጀንበር ቤት ግንባታ የጥበብ ባለውለታ ለሆነው አርቲስት ፊሻሌ ጨምሮ ለሁለት አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ በማስጀመር በወላይታ ሶዶ ከተማ መርሃ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የአንድ ጀንበር ቤት ግንባታውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፤ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴቶች ተቋማዊ የሚያደርግና ከመንግስት ይወጣ የነበረ ከፍተኛ ሀብት በማዳን ጭምር በርካቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የሚገኝ ፍፁም ሰው ተኮር መርሃ ግብር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አስጀማሪነት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአይነትም ሆነ በመጠን እየሰፋ መምጣቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መርሃ ግብሩ ሁሉን አሳታፊ በመሆኑም ዜጎች ለአወንታዊ ለውጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰብዓዊነትን የሚያስቀድምና የህሊና እርካታን የሚያስገኝ ከመሆኑም ባሻገር የዜጎችን ሕይወት ያሻሽላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በጎነት ለአብሮነት፤ ለሀገር ከፍታና ለራስ በመሆኑም በመርሃ ግብሩ ሁሉም ሊሳተፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

አክለው ያሉን የተፍጥሮ ፀጋዎች ላይ በጎነትንና ቅንነትን በማከል እርስ በርስ ከተባበርን፤ ከተጋገዝንና ከተደመርን ጊዜያዊ ችግሮቻችንን በመሻገር ባጭር ጊዜ በጥረታችን ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል።

ባለፉ ጊዜያት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የማይታለፉ የሚመስሉ ፈታኝ ወቅቶችን ከመሻገር ባለፈ የማይቻሉ የሚመስሉ በርካታ አስደናቂ ስኬቶች ማስመዝገብ የተቻለው በመተባበርና መደጋገፍ ውስጥ ባለ ኅብረትና አንድነት መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች፤ ሴቶችና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን ተጠቃሚ ያደረጉ፤ የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና አብሮነትን የሚያጎለብቱ እንዲሁም ለዘላቂ ሰላምና ልማት የጎላ ሚና ያላቸው በርካታ የበጎ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣው የበጎ ፈቃድ ተግባር ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም በሁሉም መስክ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በመደረግ ላይ ላለው ጥረት ትልቅ አቅም የሚፈጥር በመሆኑም በቋሚነት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በሚከናወነው የአንድ ጀንበር የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታም፤ 4 ሺህ 600 ቤቶችን በአንድ ጀንበር በመገንባት ሌላ አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ መታቀዱን ጠቅሰው፤ በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች ለታቀደው ግብ ስኬት ህብረተሰቡ በነቂስ በመሳተፍ የዚህ አኩሪ ታሪክ አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ጽ/ቤቱ ከሁለቱ ቤቶች በተጨማሪ በጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከተው ለአንጋፋው ድምፃዊ አርቲስት ፊሻሌ ሚልካኖ በአጭር ጊዜ ቤት ሰርቶ ከነሙሉ እቃው እንደሚያስረክብ ገልፀው፤ በቀጣይ በሁሉም ዞኖች እንዲህ አይነት የጥበብ ሰዎችን በመለየት የመደገፍ ስራ እንደሚጠናከር አስረድተዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ያለንን ጉልበት፤ ዕውቀት እና ሀብት አቀናጅተን በራስ አቅም ችግሮቻችንን ለመፍታት ከተባበርን እና በኅብረት ለጋራ ልማት ከተጋን ዘላቂ ልማትንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ይበልጥ ባጠረ ጊዜ እናረጋግጣለን ሲሉ በአጽንኦት በመግለጽ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጸ/ቤት በ2016/17 ዓ/ም የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስድስቱም የክልሉ ማዕከላት ሰባት የአረጋዊያን እና አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን አከናውኖ በማጠናቀቅ ከነሙሉ የቤት እቃ ለባለቤቶቹ ማስረከብ መቻሉ ተገልጿል፡

ጽሕፈት ቤቱ በዘንድሮም መርሃ ግብር ወላይታ ሶዶን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ባለሀብቶችንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር አስራ አንድ የአረጋዊያንና ጧሪ ያጡ አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን የሚያከናውን መሆኑም ታውቋል፡፡

በክልሉ በተመሳሳይ የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የአንድ ጀንበር ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሁሉም የክልሉ ማዕከላት፤ ዞኖች እና የተለያዩ አካባቢዎች በክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተመርተው ተከናውነዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በአርባ ምንጭ ከተማ ክልል አቀፍ የአንድ ጀንበር የቤት ግንባታ መርሃ-ግብር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አስጀምረዋል፡፡

ዶ/ር ኤርጉጌ በመርሃ ግብሩ በጎነት የኢትዮጵያዊያን ማንነት መገለጫ መሆኑን አዉስተው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወሰንና ድንበር የሌለው፤ ሰው መሆን ብቻ ቅድሚያ የሚሰጥበት የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የሚያጠናክር ከቅን አስተሳሰብ የመነጨ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ሀገር ባለፈው ዓመት በተከናወነ የበጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ መረሃ ግብር ከ24 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በ14 ዘርፎች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ በአርባ ምንጭ ከተማ 5 የአቅመ ደካማ ቤት ግንባታ እና ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ 8.5 ሚሊዮን የሚደርስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ በዕለቱ የአንድ ጀንበር የቤት ግንባታ የ6 ሚሊየን ብር ቼክ አበርክተዋል።

በመርሃ ግብሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደርና የስራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው፤ የበጎ አድራጎት ተግባራት ሰዎች ያለማንም ቅስቀሳ በጎ አመለካከታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እዉቀታቸዉንና ሀብታቸውን እሴት በሚጨምሩ ተግባራት ላይ የሚያዉሉበት በመሆኑ የወደቀውን ማንሳት፤ የተቸገረን መርዳት ከሰዉነትም በላይ ነዉና ተግባሩን ማስቀጠል ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

Leave a Reply