
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በአንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ ኢኒሼቲቭ የታተሙ ከ1ኛ – 3ኛ ክፍል ላሉ ታማሪዎች የሚውሉ መማሪያ መፅሐፍት ስርጭት በወላይታ ሶዶ ከተማ በይፋ አስጀምረዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሃ ግብሩ በ “አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ” ንቅናቄ ህብረተሰቡን በማስተባበር በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የታተሙ መፅሐፍትን ካለፈው አመት ጀምሮ ለተማሪዎች እና መምህራን ለማሰራጨት በምብቃታችን ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።
የዕድገትና የብልፅግና መሰረት ትምህርት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ያለትምህርት ብቁ ሆኖ መገኝትም ሆነ ብቁ ዜጋ ማፍራት የማይቻል በመሆኑ በዋናነት የትምህርት ዘርፉን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ካልሰራን ያለምነውን ብልፅግና ዕውን ማድረግ አንችልም ሲሉ ተናግረዋል።


በክልሉ በሁሉም የትምህርት ዕርከኖች ያጋጠመን የመፅሐፍት እጥረት በማቃለል እንደ ሀገር የገጠመንን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በማመን የጀመርነው ኢኒሼቲቪ ስኬት ተባብረን በኅብረት ከሰራን በሁሉም መስክ ውጤታማ መሆን እንደሚንችል ያሳየ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው በትምህርት ላይ ያጋጠመንን ስብራት ለመጠገን በጀመርነው ጥረት ከመምህራን፤ ከወላጆች፤ ከተማሪዎች እንዲሁም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት በመስራት የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርን ጨምሮ ትምህርት ቤቶችን በመጠገን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የ “አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ” ኢንሸቲቪ ዕውን መሆኑን ተከትሎ ምንም ካልነበረበት አንድ መፅሃፍ ለሶስት ተማሪዎች እንዲደርስ ማድረግ መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም በህብረተሰቡ ተሳትፎ የትምህርት ዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ ኢንሼቲቩን በማስተባበር ለመሩ ኃላፊዎች፤ ቅስቀሳ ላደረጉ የሚዲያ አካላት እንዲሁም ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ በክልሉ መንግስት ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ትምህርት ቤቶችን መጠገንን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን ለማሟላት በሚደረገው ጥረት የክልሉ ሕዝብ ርብርብ እንዲያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡