
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በቴክኖሎጂ የታገዘና በሀገራዊ ኢኒሼቲቮች የተቃኘ የግብርና ልማት ሥራ በማከናወን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፥ ክልሉን የሰላም፣የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
የተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመትም የክልሉን ጸጋና የልማት አቅም በጥናት በመለየት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተያዙ እቅዶች በስኬት የተጠናቀቁበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በክልሉ የግብርና ልማት ሥራዎች በሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ተቃኝተውና በቴክኖሎጂ ታግዘው የተከናወኑ በመሆናቸው ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
እንደ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ገለጻ የሃገር በቀል ሪፎርሙ ትኩረት የሆነው የግብርና ልማት ሥራ ከመደበኛ ሥራ በተጨማሪ ሃገራዊ ኢኒሼቲቮችን ማዕከል እንዲያደርግና ከልማዳዊ አሰራር እንዲላቀቅ እየተደረገ ነው።
በዚህም ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚያስችሉና የኤክስፖርትና ተኪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት በምግብ ራስን የመቻል ሀገራዊ ግብን ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ነው የገለጹት።
የበጋ ስንዴ ልማትን ጨምሮ በደቡብ ኦሞ ዞን ሩዝን የማላመድና ማሽላና በቆሎን በስፋት በማምረት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኤክስፖርት ምርቶችን ከማሳደግ አንጻር የቡና ማሳን የማስፋትና የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማላመድ ስራ በመከናወኑ ምርት መጨመሩን አቶ ጥላሁን ጠቅሰው፥ በበጀት ዓመቱ 45 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
ቅመማ ቅመምና የቅባት እህሎችን በስፋት አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎችም ውጤት እያመጡ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣በፍራፍሬ ልማትም በክልሉ ሙዝ፣ማንጎ አቮካዶ እና አፕል ምርቶችን በስፋትና በጥራት የማምረት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ክልሉ እንደሃገር የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተጀመረበት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ፕሮግራሙ በክልሉ አርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች ያለውን የእንስሳት ሃብት ልማት ምርታማነት እያሳደገ መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሮግራሙ በወተት፣ሥጋ፣ እንቁላል፣ ማርና ዓሣ ምርት ላይ የነበረውን ሃብት በተሻለ መጠቀም ያስቻለና የግብርና ስራው ዓመቱን ሙሉ እንዲከናወን እድል የፈጠረ መሆኑንም አስታውቀዋል።፡
በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተከናወኑ ተግባራትም ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉና የስራ እድል የፈጠሩ በመሆናቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ተገኝቶባቸዋል ብለዋል፡፡
አንድ ተራራን በአንድ ዞን የማልማት ክልል አቀፍ ኢኒሼቲቭም የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው አካል ሆኖ ተራሮችን ከስጋት ወደ ሃብት ምንጭነት ለመቀየር ስራዎች እየተሰሩና ውጤት እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ፥ በክልሉ የግብርና ልማት ሥራዎችን በሃገራዊ ኢኒሼቲቮችና በቴክኖሎጂ ከማገዝ ባለፈ እስከ አርሶ አደሩ ማሳ የደረሰ ተቋማዊ አሰራርን በማጠናከር የተከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ መሰረታዊ የሚባሉ የዘርፉን ችግሮች በመፍታት በተያዘው በጀት ዓመት የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።