“ብልፅግና ውስብስብ ችግሮች እና ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በሁሉም ዘርፍ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ 

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጅግጅጋ ከተማ ተገኝተው የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሃሳብ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ህዝባዊ ውይይት አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚሁ ይፋዊ የስራ ጉዳይ ጅግጅጋ ከተማ ሲደርሱ፤ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሀመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ህዝባዊ የውይይቱ መድረኩ የመደመር መንግስት ትሩፋት የሆኑ ስኬቶችና ቀጣይ ብሥራቶች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር፤ የተገኙ ድሎች ቀጣይነትን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ለማስችል ያለመ መሆኑም ታውቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በህዝባዊ ውይይቱ ወቅት፤ ብልፅግና ውስብስብ ችግሮች እና ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

አክለው የመደመር መንግሥት በሁሉም አካባቢዎች ያሉትን አቅሞች ለይቶ በማልማት ለህዝቡ ተጠቃሚነት እየተጋ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በለውጡ ዓመታት በተሰራው ስራ ስንዴ ከውጭ ማስገባት ማቆም መቻሉን አንስተው፥ በሁሉም ዘርፎች ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የሶማሌ ክልል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያለው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መንግስት ይህንኑ እምቅ አቅም ተጠቅሞ ህዝቡን በማስተባበር ለአካባቢው ሁለንተናዊ ልማት በልዩ ትኩረትበመስራት ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከህዝቡ የተነሱ የውሃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በክልሉ ከለውጡ ወዲህ ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፥ እነዚህ የልማት ሥራዎች መንግስትን የሚያስመሰግኑ ናቸው ብለዋል፡፡

መንግስት በክልሉና በከተማዋ ላከናወናቸው በርካታ የልማት ሥራዎች ህዝቡ ሰላሙን ከመጠበቅ ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች፥ ይህን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኘው መንገድ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የጠየቁት ነዋሪዎች፤ መንግሥት በተለይም ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሰጠው ትኩረት ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጅግጅጋ ቆይታቸው፤ የኮሪደር ልማት ስራ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ፤ የሸቤሌይ ሪዞርት የቱሪዝም ማዕከል የግንባታ ሂደት ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

 

Leave a Reply