
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንትናው ዕለት ለይፋዊ የስራ ጉብኝቱ አርባ ምንጭ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና በሀገር ሽማግሌዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርባ ምንጭ ቆይታቸው የሀገራዊው የ’ገበታ ለትውልድ’ አካል የሆነው የአርባ ምንጭ ኮንፍረንስ ሪዞርት ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት፤ የከተማውን የኮሪደር ልማት፤ በጋሞ ዞን አስተዳደር በጋሞ ልማት ማህበር በመልማት ላይ የሚገኘው የአርባ ምንጮች የቱሪስት መዳረሻ ልማት ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡



በጉብኝቱ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አርባ ምንጭ ከተማ ሲደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎች እንኳን ወደ ቤቶ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና በክልሉ አርባ ምንጭ ከተማ መጡ በሚል ልባዊ ፍቅራቸውን በመግለጽ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።



መሪውን ማክበር የሚያውቀው እንግዳ ተቀባዩ የአርባ ምንጭ ከተማ ህዝብ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ባለፉባቸው ጎዳናዎችና በደረሱበት የከተማው ጫፍ ሁሉ የአካባቢው የሰላምና የፍቅር መገለጫ የሆነውን እርጥብ ሳር ይዞ ልብ የሚያሞቅ አቀባበል በማድረግ ልባዊ ፍቅሩን እና አክብሮቱን ገልጿላቸዋል።



