
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ያስገነባቸውን 296 መኖሪያ ቤቶች በዛሬው ዕለት ለተጎጂዎች አስረክበዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ በርክክብ መረሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ማህበሩ አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ለተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ በማድረግ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ መሆኑን በተግባር ሲያሳይ መቆየቱን ተናግረዋል።
የተፈጥሮ አደጋ በተለይም ከክረምት ዝናብና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የመሬት መንሸራተት አደጋ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተደጋጋሚ የሚከሰት መሆኑንም ጠቅሰው፤ ለዘለቀታዊ መፍትሄዊ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አስጀማሪነት በመከናወን ላይ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡



የተለያዩ የስነ ሕይወታዊ እና ስነ አካላዊ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች፣ የተራራ ልማት ተግባራትን እና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስራዎችን በማጠናከርና ባህል በማድረግ የአደጋ ተጋላጭነትን መቀልበስ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ በአጽንኦት ተናግረዋል።
አክለው ቀድሞ መረጃ በማግኘት የመከላከል ስራዎችን ከማጠናከር ባለፈ የክልሉ መንግስት የውስጥ አቅምን በማሳደግ ፈጥኖ ለወገን ለመድረስና ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የተጀመሩ ውጤታማ የሽግግር ስራዎችን በማጠናከር ከግብ ማድረስ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።



በጎፋ አደጋው ሲከሰት ዓለም በሙሉ አዝኖ በርካቶች ለድጋፍ እጃቸውን በመዘርጋት አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ የኢትዮጵያዊያንን የመደጋጋፍና የመተባበር ህብረት እና አቅም በተግባር ያሳየ፤ ተስፋን የሰጠና ስንተባበር ማንኛውንም ችግርና ፈተና መሻገር እንደሚንችል በተግባር ያሳያ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በየትኛውም አካባቢ ለዜጎች ቀድሞ የሚደርስና በሰባዊነት ዜጎችን የሚቀርፅ ማህበር በመሆኑም አደጋውን ተከትሎ ፈጥኖ በመድረስ አጋርነቱን በተግባር ከማሳየት ባሻገር አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ያልተቋረጠ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ በክልሉ መንስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።



የክልሉ መንግስት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አፋጣኝ የነፍስ አድንና ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ የአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የክልሉ መንግስት አደጋው በደረሰ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ 150 ቤቶችን በመገንባት የከፋ ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችን የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት ፈጥኖ ለዜጎች በመድረስ ምሳሌ የሚሆን ተግባር መፈጸም መቻሉን ተናግረዋል።
ለተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ የመጨረሻ ግብ ቤት መገንባት ሳይሆን ጓዳቸውን ሙሉ በማድረግ ከራስ ተርፎ ለሌሎች መትረፍ የሚችል ሞዴል መንደር መፍጠር መሆኑንም አብራርተው፤ ማህበሩ ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም ድጋፍን በዘላቂነት እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።



ሁሌም ቢሆን ስራ በብቃት ሲሰራ የሚተች ሰው አይጠፋም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች አሉባልታና ወሬን ወደ ጎን በመተው እና ፈተና እንደሚያጠነክር በማመን ሁላችንም ትኩረታችንን ስራችን ላይ በማድረግ ለለውጥ መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በመጨረሻም ርዕሰ መስተዳድሩ የቀይ መስቀል ገንዘቡና በጀቱ አባሉ ነውና ሁሉም አባል በመሆን በበጎነት ታሪክ እንዲሰራ ጠይቀዋል።


የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቦርድ አባል አቶ አበራ ቶላ በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።



በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፕሮግራም ማህበሩ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ስልጠና በመስጠት የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በመቅረጽ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪ ማህበሩ ወጣቶችን በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ማሰማራቱን አስረድተዋል።
