
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 22ኛ መደበኛ ስብሰባውን በርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት በማካሄድ ላይ ሲሆን፤ በመጀመሪያ ቀን ውሎው የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት አመት አጠቃላይ የስራ አፈፃፀም ከመገምገሙም ባሻገር በቀጣይ የ2018 በጀት አመት ዕቅድ ዝግጅት ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡



ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በክልሉ መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ዙሪያ ሲሆን፡- የክልሉን አስፈጻሚ ተቋማት የበጀት አመቱን የስራ አፈፃፀም የዳሰሰ ዝርዝር ሪፖርት ቀርቦ ከተያዘው ግብ አንፃር በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎች፤ የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በጥልቀት ተወያይቷል፡፡
ምክር ቤቱ በበጀት አመቱ የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለሙ ዘርፈ ብዙ ውጤታማ የሰላምና ፀጥታ፤ የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች እና ፖለቲካዊ ተግባራት መከናወናቸውን ተመልክቷል፡፡



በውይይቱ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በየዘርፉ በተከናወኑ በርካታ ስራዎች ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ስኬት መሠረት የጣሉ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉም ተገምግሟል፡፡
በክልሉ በሰላምና ፀጥታ፤ በኢኮኖሚ የዕድገት ዘርፎች -በግብርና ልማት፤ በኢንዱስትሪና በማዕድን ልማት፤ በከተሞች ልማትና በተለያዩ የመሠረተ ልማት ስራዎች በተለይም በገጠር መንገድ ግንባታ፤ በትምህርትና ጤና የማህበራዊ ልማት መስኮች፤ በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎችም ዘርፎች አበረታች ውጤት መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡



በክልሉ በ2017 በንቅናቄ በተሰሩ ስራዎች በተለይም በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፤ በተራራ ልማትና ሌሎችም ስራዎች በህዝብ ተሳትፎ በተቀናጀ አግባብ በንቅናቄ በመምራት የተሻለ ውጤትና መልካም ተሞክሮ ማግኘት መቻሉም ተመልክቷል።
በበጀት አመቱ የሀብት ውስንነቶችን በመቋቋም እንዲሁም ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አሰራሮችን በመዘርጋት በተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆን መቻሉም በውይይቱ ተወስቷል፡፡
በአጠቃላይ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በተደረጉ ጥረቶችና ሌሎቸ የክልሉ መንግስት የትኩረት አቅጣጫ ተደርገው ሲከናወኑ በነበሩ ዘርፎች ውጤታማ አፈጻጸም መመዝገቡ ተገምግሟል፡፡
በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ በሁሉም መስክ ምርታማነትን ማሳደግ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ፤ በቀጣይም በህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ በዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባ ምክር ቤቱ በአጽንኦት ገልጿል፡፡


በተለይ ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን የማላቅ ተግባራት፤ የሌማት ትሩፋትና ሌሎች የልማት ኢንሼቲቮች ውጤታማ ትግበራ፤ ፍትሀዊ ገቢን በተቀናጀ አግባብ መሰበሰብ፤ በኢንቨስትመንት፤ ቱሪዝም፤ ኢንዱስትሪ ልማት፤ የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የትምህርት እና የጤና መድህን ስራዎች እንዲሁም የዲጂታል ኢኮኖሚ ተግባራት ከዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡


በመጨረሻም መስተዳድር ምክር ቤቱ የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከነማሻሻያው በማፅደቅ ለክልሉ ህዝብ ምክር ቤት እንዲመራ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል በክልሉ መንግስት ቀጣይ የ2018 በጀት አመት መሪ ዕቅድ ዝግጅት ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን በመለት በዝርዝር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ መሪ ዕቅዱ ሀገራዊ ግቦችን፤ የክልሉን የቀጣይ 7 ዓመት የብልፅግና ፎኖተ ካርታን፤ በክልሉ ህዝብ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች የተገኙ ግባዓቶች፤ ተጨባጭ የማስፈጸም አቅም እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ፀጋዎችና የመልማት አቅሞች ታሳቢ ባደረገ እና በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጠናከር የህዝቡን ሁሌንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ እንዲዘጋጅ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡