
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በ22ኛ መደበኛ ስብሰባው 2ኛ ቀን ውሎ፡- የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት አመት ረቂቅ የበጀት ቀመር፤ የአዳዲስ የልማት ኢንሼቲቮች ትግበራ ዝግጅት እንዲሁም የክልል ማዕከላት የተቋማት ህንፃ ግንባታ ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡



መስተዳድር ም/ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በክልሉ መንግስት የ2018 በጀት አመት ድጎማ በጀት ቀመር ላይ ሲሆን፤ የቀረበውን ረቂቅ የበጀት ቀመር ከፍትሃዊነትና ታዓማኒነት፣ በክልሉ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም፤ በሁሉም ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ እንዲሁም ከኢፌድሪ ፌዴሬሽን ም/ቤት የበጀት ድልድል ቀመር አኳያ በዝርዝር ገምግሟል፡፡
ምክር ቤቱ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን በቅርበት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ከጠቅላላው የክልሉ መንግስት የ2018 ዓ/ም በጀት ውስጥ፡- 20 በመቶውን ለክልል ማዕከላት እንዲሁም 80 በመቶውን ለዞን እንዲውል በሙሉ ድምፅ በመወሰን ለክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት መርቷል።



መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል በክልሉ ሀገራዊ የአዳዲስ የልማት ኢንሼቲቮች ትግበራ ዝግጅት በተመለከተ አጀንዳው፡- የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ትግበራ ዙሪያ በጥልቀት በመምከር ለውጤታማ አተገባበሩ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፤ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሁም ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት አሰጣጥ በአንድ ጣሪያ ስር ተደራሽ በማድረግ ዘርፈ ብዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚቀርፍ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የሌማት ትሩፋት መርሃግብርን ጨምሮ በክልሉ በመተግበር የሚገኙ የልማት ኢንሼቲቮች የከተማውንና የገጠሩን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የሚገኙ መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይም ለውጤታማ አተገባበራቸው የፊት አመራሩ ተገቢውን የመሪነት ሚና እንዲወጣ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
2017 የበጀት አመት በብዙ መልኩ ለክልላዊ የዘላቂ ሰላም፤ ልማትና ሁለንተናዊ ብልፅግና ግብ ስኬት መሠረት የጣሉ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑንም ጠቅሰው፤ አመራሩ በሁሉም ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን በ2018 በጀት አመት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ህዝቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ለላቀ አፈጻጸም መትጋት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡



ምክር ቤቱ በመቀጠል በክልል ማዕከላት የተቋማት ህንፃ ግንባታ ዙሪያ የተወያየ ሲሆን፡- በሁሉም የክልሉ ማዕከላት ሊገነቡ ለታሰቡ የተቋማት ህንፃ ግንባታ ቀድሞ የተጀመሩ ስራዎች የደረሱበትን ደረጃ በመገምገም፤ ግንባታውን በሁሉም ማዕከላት በፍጥነት በመጀመር ባጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በክልሉ ማዕከላት የክልል ተቋማት ህንፃ ግንባታ በክልሉ ለቢሮ ኪራይ የሚወጣ ከፍተኛ ሀብት በማዳን ለልማት ስራዎች ለማዋል የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ በተጨማሪም ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ ስብሰባውን በነገው ዕለት በመቀጠል ረቂቅ ደንቦች እና አዋጆች ላይ በዝርዝር የሚወያይ ይሆናል።