“የክልሉ መንግስት ለኦቶና ሆስፒታል መልሶ ግንባታ የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደርጋል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኦቶና ሆስፒታል ተገኝተው በሆስፒታሉ ተከሰቶ የነበረው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ያደረሰውን ጉዳት ተመልክተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚገኘው አንጋፋው የኦቶና (በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል) ሐምሌ 19 ቀን 2017 ዓ/ም የተከሰተ ድንገተኛ የእሳት አደጋ በሆስፒታሉ ላይ ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት አድርሷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እጅግ አሳዛኝ የሆነው ድንገተኛ የእሳት አደጋው በክልሉ አንጋፋ በሆነው ሆስፒታሉ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፤ በደረሰው ጉዳት ዙሪያም ከሆስፒታሉ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት ሆስፒታሉ የክልላችን ብቸኛ የኩላሊት እጥበት የሚካሄድበት እጅግ በጣም በርካታ ሰዎችን የሚያገለግልና ታማሚዎችን በመታደግ ስመጥር የሆነ ሆስፒታል መሆኑን ገልፀዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በአደጋው እጅግ ማዘናቸውን በመግለጽ ከምንም በላይ የሰው ህይወት ባለማለፉ ፈጣሪ ታድጎናል ያሉ ሲሆን፤ የወደመውን ቁስ በመተካት ሆስፒታሉ ባጭር ጊዜ በቀደመ ተቋማዊ አቅሙ ተመልሶ አገልግሎት መስጠት እንዲችል እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።  

የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የፀጥታ መዋቅሩ እንዲሁም የአጎራባች ዞኖች ባደረጉት ርብርብ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን ገልፀው፤ ላደረጉት ትልቅ ተጋድሎ እና ርብርብ የክልሉ መንግስት ምስጋናና እውቅና ይሰጣል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የክልሉ መንግስት ከክልሉ አልፎ ለቀጠናው ህብረተሰብ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው ሆስፒታሉ፥ ባጭር ጊዜ በቀደመ ተቋማዊ አቅሙ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።

ለዚህም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ የአጭር እና የረዥም ጊዜ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመው፥ የክልሉን ህዝብ የተለመደ ኅብረትና ትብብር በተጨባጭ የሚያሳይ ሀብት የማሰባሰብ ስራ የሚከናወን መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአጭር ጊዜ አኳያ የተቋረጠውን የህክምና አገልግሎት ባፋጣኝ ለመመለስ እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ ለዚህ ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ለኦቶና ሆስፒታል መልሶ ግንባታ እና ተቋማዊ አቅም ማጠናከሪያ የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ያስታወቁ ሲሆን፤ በክልሉ የሚገኙ 12ቱ ዞኖች እና ሶስቱ ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች በጋራ በወንድማማችነት ሆስፒታሉን ወደ ነበረበት ለመመለስ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል። 

በምልከታውና በውይይቱ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ የዞን አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

Leave a Reply