“የገጠሩን ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመንገድ መሰረተ ልማት ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በመሰራት ላይ ይገኛል” ርዕስ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ሶዶ ዲስትሪክት የተገነባ የገጠር መንገድ ልማት ፕሮጀክት መርቀው ከፍተዋል።

መንገዱ ከቦዲቲ ከተማ እስከ ኮናሳ ፑላሳ እንዲሁም አጎራባች ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ አቋርጦ ወደ ዋርካ የሚወስድ 20 ኪ/ሜ የሚሸፍን የገጠር መንገድ ፕሮጀክት አካል መሆኑ ታውቋል።

በዚህም የዳሞት ወይዴ፣ ቦዲቲ ከተማና ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሃ ግብሩ መንግስት ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የገጠሩን ህዝብ በርካታ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለው ለኢኮኖሚያዊና ለማህበራዊ የብልፅግና ትልም ስኬት መሰረት ለሆነው የመንገድ መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠትም ተደራሽንነቱን ለማስፋት በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

መንገድ በተለየ የኢኮኖሚያዊ ዕድገት የደምስር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ ከምርቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በቀጣይም የመንገድ መሰረተ ልማት ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው መንገድ የአካባቢውን አርሶ አደር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋድዳው ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል።

አርሶ አደሩም ምርታማነቱን በማሳደግ የመንገድ መሰረተ ልማቱን ተጠቅሞ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

መንገዱን ገንብተው ለማጠናቀቅ ለተጉ ሁሉ ምስጋና ያቁረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ መንገዱ በታለመው ልክ የአካባቢውን ዕድገት ማሳለጥ እንዲችል ህብረተሰቡ በአግባቡ ጠብቆ እንዳቆይ አሳስበዋል።

የክልሉ  ትራንስፖርትና መንገድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው፥ መንገድ የልማት ሁሉ መሰረት በመሆኑ የክልሉ መንግስት የመንገድ መሰረተ ልማት ፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 421 ኪ.ሜትር መንገድ የተጠናቀቀ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፥ ከዚህ ውስጥ ዛሬ የተመረቀው ኮናሳ ፑላሳ- ሲባዬ ቆርኬ -ጉርሞ ኮይሻ መንገድ 20 ኪ/ሜ የሚሸፍን መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ኃይለማርያም መንገዱን ገንብቶ ለአገልግሎት ላበቃው ለወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት እና ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል ላደረገው የደቡብ መንገዶች ባለስልጣን ምስጋና አቅርበዋል።

Leave a Reply