
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምክር ቤት እና የብሔረሰቦች ምክር ቤት 6ኛው ዙር 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በአርባ ምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡



ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ የክልሉ ሕዝብ ምክር ቤትና የብሔረሰቦች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመክፈቻ ንግግራቸው መግቢያ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመላ ኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ አጠናቀን በዓለም አደባባይ ታላቅ ብሔራዊ ድል በመጎናጸፍ የሀገራችንን የዘመናት የቁጭት ምዕራፍ ዘግተን በኢትዮጵያ የማንሠራራት ምዕራፍ ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡



በመላ ኢትዮጵያዊያን የተደመረ አቅምና የዓላማ ጽናት ለድል የበቃው ሕዳሴ ከፕሮጀክት በላይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ፕሮጀክቱ ከረዥም እንቅልፍ አንቂ፤ የሀገራችንን የንጋት ዘመን አብሳሪ፤ የአርበኝነት መገለጫና ድህነትን ድል መንሻ የሉዓላዊነት ማስከበሪያ መሳሪያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ሀገር አሻጋሪ የሆነው ሕዳሴን ከገባበት ቅርቃር አውጥተው መላ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር በታላቅ ትጋት፤ በጽናትና በቁርጠኛ አመራር ከዳር ላደረሱት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡



ከዚህም በላይ ወቅቱ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ባጫር ጊዜ በማረጋገጥ ከተረጅነት ወደ ረጅነት የሚያሸጋግረን የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መሰረት የተጣለበት እና የከርሰ ምድር ሀብታችን የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ ወጥቶ አይቀረ የሆነው የኢትዮጵያን ብልጽግና በተጨባጭ የተመላከተበት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን በተሸጋገርንበት፤ ተስፋችን ወደ ሚታይና ሚጨበጥ ተለውጦ ወደ ስራ በገባንበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፤ በ2018 ኅብረት ትብብራችንን አጠናክረን፤ ያሉንን አቅሞች በመጠቀም በፈጠራና በፍጥነት ሌላ ታሪክ ለማስመዝገብ የሚንረባረብበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፉ ጊዜያት በክልሉ በመደመር እሳቤና መንገድ በመመራት በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በሁሉም የልማት አውታሮች በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ስራዎች አመርቂ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ለተመዘገበው ውጤት የሰላምና የልማት አርበኛ የሆነው ክልሉን ህዝብ አመስግነዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ የመክፈቻ ንግግራቸው የክልሉን መንግስት የ2018 የልማት ዕቅድ በዋና ዋና የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ በማተኮር የሚያቀርቡና የትኩረት አቅጣጫዎችንም የሚያስቀምጡ ይሆናል፡፡




