የክልሉ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በ22ኛ መደበኛ ስብሰባው ቀሪ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በ22ኛ መደበኛ ስብሰባው ቀሪ አጀንዳዎች ላይ በመምከር የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ አስቀድሞ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለትም በቀሪ የ22ኛ መደበኛ ስብሰባ አጀንዳው:- በቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች እና አዋጆች ላይ በዝርዝር የተወያየ ሲሆን፥ እነዚህም፡-

*በክልሉ የሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች የአደረጃጀትና አሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የወጣ ደንብ፣

*የፍርድ ቤቶች ዳኝነት ክፍያ ለመወሰን የወጣ ደንብ፣

*ክልልዊ የፍልሰት ምክር ቤት እና የትብብር ጥምረት ለማደራጀት የአሰራር ስረዓት ለመወሰን የወጣ ደንብ፣

*የማዕድን ስራዎች አማካሪ ምክር ቤት ማቋቋሚያና ተግባርና ሃላፊነት መወሰኛ ደንብ፤

*የማህበራዊ ፍርድ ቤቶች አዋጅ፣

*የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለማቋቋም እና እውቅና ለመስጠት የወጣ አዋጅ፣

*የሼሪሃ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ፤

* የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን የወጣ አዋጅ፤

በዚህም ምክር ቤቱ በቀረቡ 4 ረቂቅ ደንቦች እና 4 አዋጆች ላይ በጥልቀት በመወያየት በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በህግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ደንቦችን ከነማሻሻያቸው ያፀደቀ ሲሆን፤ የቀረቡ አዋጆችን መርምሮ ለምክር ቤት መርቷል።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት በክልሉ ተዘጋጅተው ስራ ላይ የሚውሉ የህግ ማዕቀፎች ስራዎችን በጠንካራ ተቋማዊ አሠራር፥ በፍትሀዊነት፥ በግልጸኝነትና በተጠያቂነት ማዕቀፍ በመምራትና በመፈፀም ለተሻለ ውጤት ከማብቃቱም ባሻገር ክልሉን በትክክለኛ መስመር ላይ እንዲገኝ ማስቻሉን አብራርተዋል።

በቀጣይም ጠንካራ ተቋማዊ አሠራርንና ተቋማትን መገንባት የሚያስችሉ ብሎም በተሻለ ውጤታማነት ክልላዊ ራዕዮችንና የልማት ግቦችን በማሳካት የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎችን ስራ ላይ በማዋል የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም ከቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር አያይዘው:-

የክልሉ መገለጫ የሆነው የሰላም ተምሳሌትነትን የማስቀጠል፥ የውስጥ አንድነትን በማፅናት የልማት ትብብሮችን የማጠናከር፥ ምርታማነትን የማላቅ፥ የምርት አቅርቦትና ትስስር ስራዎችን በማጠናከር ገበያ የማረጋጋት፥ ፍትሃዊ ገቢን በመሰብሰብ የውስጥ አቅምን የማጎልበት እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራ ስራዎችን የማጠናከር ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አያይዘው በማስገንዘብ  ስብሰባው ተጠናቋል።

Leave a Reply