
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ 2017 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ እና የ 2018 ጠቋሚ ዕቅድ መድረክ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላት እውቅና በመስጠት ተጠናቋል።



የብልጽግና ስራ አስፈፃሚ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ማጠቃለያ በመገኘት የቀጣይ ጊዜያት አቅጣጫና የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ብልጽግና ለማመን የሚያስቸግሩ ፈተናዎችን እየተሻገረ እንዲሁም ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ ዕድል እየቀየረ ከአፍሪካ ኃያል ፓርቲዎች አንዱ መሆን መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ገልፀዋል።



በዓመቱ መጀመሪያ የተካሄደው የፓርቲዉ ጉባኤ መሪ ቃል “ከቃል እስከ ባህል” መሆኑን አስታዉሰዉ ቃላችንን የምንናገር ብቻ ሳይሆን በተግባር የምንፈፅም ልንሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
2018 ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን በመሸጋገርና የታሪክ እጥፋት በማስመዝገብ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ሊሳኩ ይገባል የተባሉ ዕቅዶችን ቀድሞ ማሳካት አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት ገልፀዋል።
ብልጽግና ባለፉት ሰባት ዓመታት በሀገር ደረጃ ከገባንበት ችግር መንጭቆ ያወጣ ታላቅ ፓርቲ መሆኑንም በንግግራቸው አንስተዋል።


ጠንካራ ፓርቲ ካለ ዉጤት ማምጣት እንደሚቻል እየተመዘገበ ያለው ዉጤት አመላካች መሆኑን የጠቅሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት በማድረጉ ጉዞ የፓርቲዉ አመራሮችና አባላት ሚና የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
የተገኘው አንፃራዊ ዉጤት የተሻለ ስራ እንዲንሰራ የሚያነሳሳ እንጂ የሚያኩራራ አለመሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የፓርቲው አመራሮች በሶስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ርዕሰ መስተዳድሩ ቀጣይ አቅጣጫ ሰጥተዋል፦


የአመራሩን የዉስጥ አንድነት ማጠናከርና ለምንም የማይበገር አመራር መፍጠር፣ ጠንካራ ፓርቲ በአሠራር እንዲተከል ማድረግ እንዲሁም መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስታዊ ስራዎችን አፅንኦት ሰጥቶ መፈፀም ከፓርቲው አመራሮች እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።



ወላይታ ዞን በክልሉ ከሚገኙ መዋቅሮች በፓርቲ ስራዎች የላቀ አፈፃፀም በማስመዝገብ የዋንጫና ሰርተፊኬት ተሸላሚ ሲሆን፤ ጌዴኦ እና ጋሞ ዞኖች ሁለተኛና ሶስተኛ በመዉጣት ከርዕሰ መስተዳድሩ ሽልማት ተቀብለዋል።


የአርባ ምንጭ ኢኮኖሚ ክላስተር ቁጥር ሁለት ህብረት በክልሉ ካሉ 10 ህብረቶች በዓመቱ የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፓርቲና መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዞኖችና ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች የፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት አመራሮች፣ የህብረት ሰብሳቢዎች ተሳታፊ ሆነዋል።