
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በጉብኝታቸው በክልሉ በአርባ ምንጭ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡



ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የአርባ ምንጭ ቆይታቸው በተለይ የሀገራዊው የ’ገበታ ለትውልድ’ አካል የሆነው የአርባ ምንጭ ኮንፍረንስ ሪዞርት ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት፤ የከተማውን የኮሪደር ልማት፤ በጋሞ ዞን አስተዳደር በጋሞ ልማት ማህበር በመልማት ላይ የሚገኘው የአርባ ምንጮች የቱሪስት መዳረሻ ልማት ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡



ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርባ ምንጭ የነበራቸውን ቆይታ ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-



የአርባምንጭ በተፈጥሮ ስሪቷ ውብ ናት።
በከተማዋ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ሥራዎች በቅርቡ በጎበኘንበት ወቅት የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክትን ተመልክተናል። ይኽ ሥራ በመጠነ ርዕዩ ግዙፍ በመሆኑ አርባምንጭ ታላላቅ ጉባኤዎችን እንድታስተናገድ ያስችላታል። ከዚህ ቀደም ከነበረን ምልከታ ሰፋ ብሎ የተከናወነው የኩልፎ ወንዝ ዳርቻ ልማት ለከተማዋ ልዩ መልኮች ተጨማሪ ገጽታ ፈጥሯል።



ወደ አርባምንጭ ጫካ አዳዲስ የመግቢያ መንገዶች የተሠሩ ሲሆን ለተራሮቹ፣ ለውሃው እና ለከባቢው ደኖች መዳረሻ በር ሆነዋል። እነዚህና ሌሎች ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ብዙ ከተሞች ያየናቸው መሻሻሎች የተለያዩ አማራጮች እንዳሉን የሚያሳዩ ያልተጠቀምንባቸውን አቅሞቻችንንም የሚገልጡ ናቸው። ይኽ እድገት በጋራ ጥረቶቻችን ታላላቅ ነገሮችን እንደምናሳካ የሚያመለክት ግልጽ ምልክት ነው።





