
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በዚሁ 24ኛ መደበኛ ስብሰባው፡-
የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም በመገምገማ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ፣ በታችኛው የአስተዳደር እርከን የአስፈጻሚ አካላት የስልጣን እና ተግባር የመዋቅር ማሻሻያ እንዲሁም የቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች መርምሮ ማፅደቅን ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ ውሳኔ የሚሹ ተያያዥ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔ አሳልፋል፡፡



መስተዳድር ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በታችኛው የአስተዳደር እርከን የአስፈጻሚ አካላት የስልጣን እና ተግባር የመዋቅር ማሻሻያ በተመለከተ የቀረበ በጥናት ላይ የተመሰረተ የፕሮጀክት ረቂቅ ላይ ሲሆን፤ ረቂቁን ክልላዊ የልማትና የብልጽግና ትልሞችን በውጤታማ አፈጻጸም በማሳካት የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በዝርዝር ገምግሟል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት፡- ከዚህ ቀደም የክልሉን አስፈፃሚ አካላት የስልጣን እና ተግባር የመዋቅር ማሻሻያ ለመወሰን የወጣ አዋጅ በምክር ቤት ጸድቆ በትግበራ ሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡



አክለው ይሄኛው ረቂቅ ጥናት በታችኛው የአስተዳደር እርከኖች የልማት ግቦችን በተሻለ ውጤታማነት ከማሳካት በተጨማሪ የዞን እና የሪጂኦ ፖሊስ ከተሞች አስተዳደራዊ መዋቅር ከክልሉ አስፈጻሚ ተቋማት አደረጃጀት ጋር ተናቦ መሄዱ አስፈላጊ በመሆኑ ጥናቱ መደረጉን አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ አላስፈላጊ የስራ መደራረብን እና የሀብት ብክነትን በሚቀንስ እንዲሁም ውጤታማነትን በሚያሳልጥ መልኩ የክልል፣ የዞን፣ የሪጂዬ ፖሊስ ከተሞች፣ የወረዳና ሌሎች የአስተዳደር እርከኖችን በፈርጅ በመለየት የአስፈፃሚ አካላት በአዲስ መልክ የማዋቀር ስራ መሰራቱንም አብራርተዋል፡፡



አደረጃጀቱ በክልሉ የሚመደበውን ውስን ሀብት በአግባቡ ለስራ ለማዋል የሚያግዝ፤ የህዝቡን አዳጊ የመልማት ፍላጎት በብቃት ለመመለስ የሚያስችል እንዲሁም ክልላዊ የሰላምና የብልጽግና ራዕይን ባጠረ ጊዜ ለማሳካት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።


ምክር ቤቱ የክልሉ ምስረታን ተከትሎ በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች አስፈጻሚ አካላትን በማዋቀሩ ሂደት ከነባሩ ክልል የተወረሰ መዋቅር በስፋት በመተግበሩ አላግባብ የተለጠጠ የአስፈጻሚ አካላት መዋቅር ክልሉን ለአላስፈላጊ የሰው ሃይል ብክነት እና ለከፍተኛ አስተዳደራዊ ወጪ መዳረጉን በመገምገምና ፋይዳውን በማጠን የቀረበውን ረቂቅ አጽድቋል፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል በዝርዝር የተወያየው በቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች ላይ ሲሆን፡-
* የአስፈፃሚ አካላት የመዋቅራዊ አደረጃጀት ለመወሰን የወጣ ደንብ፤
* የመሶብ የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት ለማቋቋም የወጣ ደንብ፤
* የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችን መከታተያ አስተዳደር ጽ/ቤት ደንብ፤
ምክር ቤቱ በቀረቡ ረቂቅ ደንቦችና አዋጆች ላይ ተወያይቶ በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በህግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ደንቦችን ከነማሻሻያቸው አፅድቋል።
መስተዳደር ምክር ቤቱ በተጨማሪም በክልሉ በበጀት አመቱ በየዘርፉ የተጣሉ የሰላም፤ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦችን በህዝቡ ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ለላቀ ውጤት መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጿል፡፡



ለዚህም ምክር ቤቱ ሰላምን የማጽናት፥ ግብርናን የማዘመን፤ የሌማት ትሩፋት፤ መስኖ ልማት፤ የገቢ አሰባሰብ፤ የዋጋ ንረት ቁጥጥርና ክትትል፣ ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለትምህርትና ጤና፣ ቱሪዝም፤ አምራች ኢንዱስትሪና ማዕድን ልማት፤ ለከተሞች ልማትና የገጠር ኮሪደር እንዲሁም በንቅናቄ የሚከናወኑ ተግባራትን የማጠናከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ርዕሰ መስተዳድሩ በየደረጃው ያለው አመራር ከህዝብና ከመንግስት የተጣለበትን ታላቅ ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት፤ ፈጠራና ፍጥነት በታከለ አግባብ በበጀት ዓመቱ የተሰነቁ ግቦችን ያለምንም መሸራረፍ በመፈጸምና በማስፈጸም ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የብልጽግና ግብ ስኬት አቅም የሚፈጥሩ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።




