የክልሉ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 25ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በአርባ ምንጭ ማዕከል ባካሄደው 25ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በወቅታዊ አስቸኳይ የጤና ጉዳይ በተመለከተ አጀንዳው ላይ ሲሆን፤ በዚህም በክልሉ በጅንካ ከተማ በተከሰተው ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ባለው የሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ (Hemorrhagic Fever) ዙሪያ በመምከር ስርጭቱን ለመግታት እንዲሁም ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከተል ለመቆጣጠር የሚያስችል ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

የክልሉ መንግስት በጤናው ዘርፍ ከፌዴራል መንግስት እና ከአጋር አካላት ጋር ጥራት ያለው ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽትን ለማስፋት በማድረግ ላይ ካለው ጥረት ባለፈ፤ የጤና አደጋዎች እንዳይከሰቱ የመከላከልና ከተከሰተም በአፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ስራዎች እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

በጅንካ የበሽታውን መከሰት ያመላከቱ የቅኝት መረጃዎች መገኘት ተከትሎ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ጋር አፋጣኝ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱም የተገለጸ ሲሆን፤ በሽታው ሰብዓዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በማስከተል የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ፈጣን ምላሽ ሰጪ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑ ተመልክቷል።

አሁን ላይ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንኪኪ የነበራቸውን ግለሰቦች በመለየት በጊዜያዊ ለይቶ ማቆያ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ከመሆኑም ባለፈ፤ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል ለመከላከል የክልሉ መንግስት የፈጣን ምላሽ መስጫ ማዕከል ጅንካ ላይ ተቋቁሞ ከፌደራል ድንገተኛ በሽታ የመከላከል ቡድን ጋር የተቀናጀ ተግባራት በማከናውን ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ምክር ቤቱ ህብረተሰቡ በሽታው በቀላሉ በንኪኪ የሚተላለፍ መሆኑን በመገንዘብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳሰበ ሲሆን፤ በየጊዜው በሽታውን የተመለከተ አስፈላጊ መረጃ በፌደራል ጤና ሚንስቴር በኩል ብቻ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡

መስተዳደር ምክር ቤቱ በተጨማሪም በክልሉ በበጀት አመቱ በየዘርፉ የተጣሉ የሰላም፤ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦችን በህዝቡ ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ለላቀ ውጤት ለማብቃት በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጿል፡፡ 

በዚህ ረገድ በተለይ የሰላምና ፀጥታ ተግባራትን በማጠናከር የክልሉ መለያና መገለጫ የሆነው የሰላም ተምሳሌትነትን የማስቀጠል፥ የገቢ መሰረቶችን በማስፋት የውስጥ ገቢን የማሳደግ፤ አላስፈላጊ የወጪ ቅነሳና የበጀት አጠቃቀም፤ መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥን የማስፋት እንዲሁም በንቅናቄ የሚከናወኑ ተግባራትን የማጠናከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በተጨማሪም ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን አጠናቋል።

Leave a Reply