ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን መንግስት የ2018 የግማሽ ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ           

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባዔውን በአርባ ምንጭ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ምክር ቤቱ የካቲት 06 እና 07/2018 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚሁ ጉባኤው፡-

የክልሉን መንግስት የ2018 የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፤ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የሚቀርቡ -ክልላዊ ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር የክልሉን ሕዝብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ የተዘጋጁ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ማፅደቅን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የክልሉን የሰላምና የልማት ውጤታማ ተግባራት የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

በጉባኤው የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡         

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው መክፈቻ፡- በክልሉ በጅንካ ከተማ ተከስቶ የነበረው የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በተደረገ ውጤታማ የተቀናጀ ርብርብ ተጋርጦ የነበረው አደጋን በመቀልበስ መቆጣጠር መቻሉ በታወጀበት ማግስት ጉባኤው መደረጉን ጠቅሰው፤ ርብርብ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፉ የለውጥ አመታት መዳረሻውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ያደረገው የለውጡ መንግስት፤ በመደመር ዕሳቤና መንገድ እየተመራ እንደ ሀገር የታሪክ እጥፋት ያስመዘገቡ፤ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ በማይቀለበስ መሰረት ላይ ያስቀመጡ አያለ ስኬቶች ማስመዝገብ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡ 

በተለይም በክቡር ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፤ ቆራጥ ስትራቴጂካዊ አመራር ሀገራዊ የተፈጥሮ ፀጋዎችን ታሳቢ ያደረጉ ኢንሼቲቦችን በመተግበር፤ በአጭር ጊዜ የምግብ ሉዓላዊነታችንን የሚያረጋግጡ እና የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ያፋጠኑ አስደናቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ፤ የበጋ ስንዴ ልማትን ጨምሮ በታሪካዊው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ማዕቀፍ የተመሩና የአይቻልም አስተሳሰብን የሰበሩ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በአረንጓዴ አሻራ፤ በኮሪደር ልማት፤ በቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት፤ በማዕድንና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገቡ አስደማሚ ስኬቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው የክልሉ መንግስት ክልላዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን እና የክልሉን ፀጋና እምቅ የመልማት አቅም ታሳቢ ያደረገ መሪ ዕቅዱን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች መዋቅራዊ ለውጥ ከሚያመጡ ሀገራዊ ግቦች ጋር በማቀናጀት ባለፉት 6 ወራት ለተጣሉ ግቦች ስኬት የተቀናጀ ርብርብ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በግማሽ የበጀት አመቱ የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለሙ ዘርፈ ብዙ ውጤታማ የሰላምና ፀጥታ፤ የመልካም አስተዳደር፤ የማህበራዊ ልማት እና የኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲሁም ፖለቲካዊ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በግማሽ የበጀት ዓመቱ በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በሁሉም የልማት አውታሮች በተከናወኑ በርካታ ስራዎች፤ ለክልላዊ የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ራዕይ ስኬት መሠረት የጣሉ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ ኢንሼቲቮችን ከክልላዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አቀናጅቶ በመተግበር በአመራሩ የተቀናጀ ድጋፍ፤ በባለሙያው ትጋት እና በልማት አርበኛው የክልሉ ህዝብ ተሳትፎ በሁሉም ዘርፍ የሀብት ብክነትን የቀነሰና የአፈጻጸም ፍጥነትን የጨመረ ዘላቂ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ውጤት መመዝገቡንም ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስት በሁሉም ዘርፍ ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይም የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የፈጠረውን ዕድል ተጠቅሞ አሳታፊና አካታች የኢኮኖሚ ግንባታን እውን በማድረግ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ዘላቂ ልማት በማስመዝገብ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት የትኩረት ዘርፍ ለሆነው ግብርና ልዩ ትኩረት በመስጠት በክልሉ ያሉ የመልማት አቅሞችና ፀጋዎች በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል፤ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የታገዘ ግብርናን አቅዶ በመተግበር በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡንም ጠቁመዋል፡፡ 

በግማሽ የበጀት አመቱ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይ በትምህርት ዘርፍ የህብረተሰብ ተሳትፎ የግብዓት አቅርቦትን የማጠናከር፣ በጤናው ዘርፍም የጤና መድህን ሽፋንን የማሳደግ፤ ተላላፊ በሽታዎችንና ወረርሽኝን የመከላከል እና ሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎትን የማሻሻል ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉንም ገልፀዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በዋና ዋና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች፡- በግብርና፤ ስራ ዕድል ፈጠራ፤ ትምህርትና ጤና፤ ኢንቨስትመንት፤ መሠረተ ልማት፤ ገቢ እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ እና መልካም አስተዳደር ዘርፍ በበጀት አመቱ በተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች ላይ በማተኮር ዝርዝር ሪፖርት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply