ፖሊስ የሕገመንግስታዊ ሥርዓቱ ዋልታና የዜጎች ደህንነት ዋስትና ብቻ ሳይሆን ወሳኝ የልማት ኃይል ነው- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ  

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን በ2ኛ ዙር ያሰለጠናቸው 594 የፖሊስ መኮንኖችን በምዕራብ አባያ ጊዜያዊ የፖሊስ ማስለጠኛ አስመርቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ የክልሉ መንግስት ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ሰንቆ፤ ለሰላምና ፀጥታው ዘርፍ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎች በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ከመቻሉም ባሻገር በሁሉም የልማት አውታሮች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የፖሊስ ተቋማትንና የፀጥታ መዋቅሩን ተቋማዊ አቅም የሚያጠናክሩ የሪፎርም ስራዎችን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የፖሊስ ተቋማትን ብቃት ባለው የሰው ኃይል ለማጠናከር በቁርጠኝነት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

በዛሬው ዕለት በሙያዊ ክህሎትና ስነ-ምግባር፤ በአካል ብቃት፤ በአእምሯዊ ጥንካሬ እንዲሁም በስነ-ልቦናዊ ዝግጅት የላቀ ብቃት ያላቸው እጩ የፖሊስ መኮንኖችን ባጭር ጊዜ ውስጥ በማስልጠን ለምረቃ ማብቃት መቻሉ ለዚህ በቂ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፖሊስነት ለዜጎች ደህንነት ራስን አሳልፎ ሰጥቶ በጀግንነት ህዝብን የማገልገል እጅግ የተከበረ ሙያ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ስልጠናውን በተሻለ ተወዳዳሪነት ከሌሎች ተመርጠው በመከታተል በብቃት አጠናቀው ለምረቃ ለበቁ ሰልጣኞች፣ ለአሰልጣኞች እና በስልጠናው ወቅት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ የተመረቁ ፖሊሶች በክልሉ ያለውን የሞኮንኖች ቁጥር ከፍ ማድረጋቸው ጠቅሰው የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ ህዝብን የሚያስቀድምና የሰላሙ ባለቤት የሚያደርግ፣ በዓዕምሮው የበሰለ፤ በስነ-ምግባሩ የታነፀና ወትሮ ዝግጁ የሆነ የፖሊስ ሃይል ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል።

አክለው ጠላት በተለያየ ግዜ የተለያየ እቅድ እያወጣ የፀጥታ ሀይሉን በስነ ልቦና የበላይነት ለመያዝ የሚያደርገውን ሙከራ  ለማክሰም የክልሉ ፖሊስ ለሕዝብና ለሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ የታመነ፣ በስነ ልቦና የበለይነትን የያዘ ፣ መሰረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የሚያከብርና የሚያስከብር፣ የዜጎችን ህይወትና ንብረት ለመጠበቅ ቁርጠኛ የሆነና ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

ፖሊስነት የህብረትና የአንድነት ሳይንስ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተናጠል ሳይሆን በጋራ ሲከድ ሁሌም አሸናፊ መሆን የሚቻል በመሆኑ ተመራቂዎች ህብረተሰቡን በፍጹም ሙያዊ ስነምግባርና ቅንነት እንዲሁም በመተሳሰብና  በአንድነት መንፈስ ለማገልገል መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የፖሊስ ኃይል የሕገመንግስታዊ ሥርዓቱ ዋልታና የዜጎች ደህንነት ዋስትና ብቻ ሳይሆን ወሳኝ የልማትና የእድገት ኃይል መሆኑንም ገልፀው፤ እጩ የፖሊስ መኮንኖች ሙያው በምጠይቀው ልክ ብቁ ሆነው ቀጣይ በሚሰማሩበት ፖሊሳዊ ኃላፊነት በዚው ልክ ለማገልገል ራሳቸውን ማዘጋጀት የሚገባቸው መሆኑን አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ የተመረቁ ፖሊሶች ከፊታችሁ ድህነትን የማሸነፍ ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው በቀጣይም በክልሉ ጊዜያዊና ወቅታዊ ፈተናዎችን በብቃት መሻገር የሚችል የፖሊስ ሰራዊትና ጠንካራና የማይበገር የፀጥታ ተቋም ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮ 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክሪያሳያዊ ሆኖ ምንም አይነት ኮሾታ ሳይፈጠር በማጠናቀቅ ስልጣን በህዝብ ድምፅ ብቻ እንደሚያዝ ለማሳያት የፀጥታ አካላት ትልቁን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው በመግለፅ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።

የክልሉ መንግስት የክልሉ ሕዝብ መለያ እና የክልሉ መገለጫ የሆነው ሰላምን በማፅናት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በማድረግ ላይ ባለው ጥረት፤ ህዝቡን ባለቤት ያደረጉ ዘርፈ ብዙ የሰላምና ፀጥታ ስራዎችንና የሰላም ግንባታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡  

ከዚህም ባለፈ ሕግና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በመጠበቅ እና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ በማረጋገጥ የዘላቂ ልማት ተግባራትን ለማሳለጥ የክልሉን የፀጥታ ተቋማት ተቋማዊ አቅም የሚያጎለብቱ ተከታታይ ስራዎች በመስራት ላይም ነው፡፡ 

የዚሁ አካል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የፖሊስ ተቋማት ለህሊናቸውና ለሕገ-መንግስቱ በታመኑ፤ በሙያዊ ስነ-ምግባራቸው በታነጹና እና የህብረተሰቡን ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት መፈጸም በሚችሉ የፖሊስ መኮንኖች ለማጠናከር በዛሬው ዕለት 594 የ2ኛ ዙር እጩ ሰልጣኞችን አስመርቋል፡፡

Leave a Reply