
የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል ።
በክቡር ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ሰብሳቢነት የተካሄደው የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን ሰላም በማፅናት የክልሉን አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ ያለሙ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ የክልሉ መንግስት በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ በኢኮኖሚ የበለፀገ፣ በፖለቲካ የጠነከረና የተረጋጋ እንዲሁም ሰላምና ፀጥታው የተረጋገጠ ምሳሌ መሆን የሚችል ክልል ለመገንባት በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ባለፉ ጊዜያት ሰላምን ቀዳሚው አጀንዳ በማድረግ ዘርፈ ብዙ የሰላምና የፀጥታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጉባኤው የተከናወኑ ስራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በማጠን ለቀጣይ ስራዎች አቅም የሚፈጥርና የክልሉን ሰላም ለማፅናት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡



በባለፈው ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ተከትሎ በህብረተሰቡ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በተከናወኑ በርካታ ስራዎችም ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ክልሉ ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይና የታለሙ የልማት ስራዎችን ከዳር በማድረስ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የፀጥታ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንዲመገባ አስገንዝበዋል፡፡
ሰላም ስለተመኘን ሳይሆን ስለሰራን የሚመጣ ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ባለፉ ጊዜያት በፀጥታና እና ደህንነት ተቋማት ላይ ውጤታማ የሪፎርም ስራዎችን ጨምሮ የሰላም እሴቶችንና ማህበራዊ ተቋማት በመጠቀም መሰራቱ በክልሉ ማስመዝገብ ለተቻለው አንፃራዊ ሰላም ድርሻው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።



በተከናወኑ ውጤታማ ስራዎችም ዛሬ ላይ ክልሉ የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት ብቻ ሳይሆን፤ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነበት በመሆኑ ተንቀሳቅሶ ለመስራት፣ ለኢንቨስትመንትና ቱሩዝም ምቹ ሁኔታ መፍጠር በመቻሉ የክልሉን የኢኮኖሚ እንቀስቃሴ ከማነቃቃት ባለፈ ተመራጭነቱን በእጅጉ ማሳደግ መቻሉንም አብራርተዋል።
ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ለሰነቅነው ራዕይ ስኬት፤ በክልሉ ያለን ብዝኃነትና የህዝቦች ዘመን የተሻገረ አብሮትና አንድነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተካናወኑ ባሉ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እየተመዘገቡ ያሉ አመርቂ ውጤቶች አልጋ በአልጋ በሆነ አግባብ የተገኙ አለመሆኑንም ገልፀዋል፡፡



በዚህ ረገድ የክልሉ ህዝቦች አብሮ የማደግና የመልማት ትልም እና እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች የሚያማቸው ዕኩይ ዓላማ ያነገቡ አካላት፤ የክልሉን አንጻራዊ ሰላም ለማደፍረስ መጣራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሰላምን የማፅናትና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለፀጥታ ስራዎች ውጤታማነት የአመራሩ ቁርጠኝነት የመጀመሪያው መሆኑንም ገልፀው፤ አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት በመስራት እና በየወቅቱ ጊዜ የማይሰጡ የፀጥታ ጉዳዮችን በመለየትና ለመፍትሄው በቁርጠኝነት በመስራት ሰላምን ማፅናት የሚገባው መሆኑን በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡
አክለው ሰላምን ለማፅናት የፀጥታ መዋቅሩን ማጠናከር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ለህገ መንግስቱ ታማኝ ፣ በስነ ልቦና እና ስነ-አካል የበላይነት የያዘ፤ ወትሮ ዝግጁ የሆነ የፀጥታ ኃይል የማደራጀት ተግባሩን ማጠናከር የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በማድፍረስ የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል በሚሞክሩ አካላት ላይም አስተማሪ ህጋዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ ጀምሮ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከርና በመዋቅሮች መካከል ትብበርና ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት የክልሉን ሰላም ማፅናት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጉባኤው የተገኙት በኢፌዲሪ የመከላከያ ሰራዊት የደቡብ ዕዝ አዛዥ መ/ጀነራል ሰለሞን ኢተፋ በበኩላቸው፤ በክልሉ የውስጥ ሰላምን ለማስጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልፀው፤ ሰላምን ለማፅናት ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉን ፀጥታ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቁልፍ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት በመስራት አስፈላጊ ድጋፎችን የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችሉ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ጉባኤውን አጠናቋል፡፡






