
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን፤ ሁምቦ ወረዳ ሶልካ ተራራ ላይ ችግኝ ተክለው አሻራቸውን በማኖር በክልሉ የዘንድሮ የሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላን በይፋ አስጀምረዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ መርሃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት አረንጓዴ አሻራ የአካባቢ ደህንነትን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የደቀነብንን ስጋት ለመግታትና በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡



መርሃ ግብሩ የተራቆተ ሥነምህዳር መልሶ በማልማት፤ የአፈር ለምነትን በመጨመር እንዲሁም የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሃብታችንን በማጎልበት ተፈጥሮን ከማከምና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን ለመከላከል ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ የአረንጓዴ አሻራና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች ካላቸው የማይተካ ሚና አንጻር፤ ከአንድ ቀን ዘመቻ ባለፈ ህብረተሰቡን ባለቤት ባደረገ መልኩ አቀናጅቶ በመምራት እና ባህል ለማድረግ በመስራት ቀጣይነታቸውን በዘላቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡



ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክልላችን የተለያዩ ቦታዎች የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ምድር በእንክብካቤ ጉድለት መታመሟን የሚያሳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መፍትሄው የአረንጓዴ አሻራ ስራችንን የህልውና ጉዳይ በማድረግ አጠናክሮ በተደራጀ መልኩ ማከናወን መሆኑን ገልፀዋል፡፡



የክልሉ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀው፤ ዘንድሮ በክልሉ ከመቸውም ጊዜ በላይ በበልግና በተያዘው ክረምት ከ380 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቄሜታ ያላቸው ችግኞች ለመትከል ርብርብ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡



የዚሁ አካል በዛሬው ዕለት በመከናወን ላይ በሚገኘው የአንድ ጀንበር ተከላ፤ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በክልሉ 60 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለሀገራዊው የ700 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ግብ ስኬት ጉልህ አስትዋጽኦ በማበርከት አዲስ ታሪክ እናስመዘግባለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡



በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስጀማሪነት በ2011 ዓ.ም መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በህዝብ ዘንድ ዛፍ የመትከል ባህል እያበበ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ደህንነቱ የተጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ለመጪው ትውልድ ማሻገር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡



ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ የማፅደቅ ተግባር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡



በክልሉ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች በህብረተሰቡ ባለቤትነት ከ419 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት ላይ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን፤ የክልሉን የደን ሽፋንም ከ23 በመቶ በላይ በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡



በዛሬው የአንድ ጀንበር ተከላም መላው የክልሉ ህዝብ ከታዳጊ እስከ አዋቂ በየአካባቢው በተዘጋጁ ችግኝ መትከያ ቦታዎች ማላዶ በመገኘት በመትከል ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ ስኬት አሻራቸውን እንዲያኖሩና ሌላ አዲስ ታሪክ እንዳስመዘግቡ ርዕሰ መስተዳድሩ ዳግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡