ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የኦቶና ሆስፒታል መልሶ ሟቋቋም ግብረ ሀይል የስራ እንቅስቃሴ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀመጡ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በአንጋፋው የኦቶና ሪፈራል ሆስፒታል የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ ባጭር ጊዜ በቀደመ የተሟላ ተቋማዊ አቅሙ የተሻለ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማስቻል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ ሀይል በማቋቋም የስራ ስምሪት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በግብረ ሀይሉ ባለፉ 72 ሰዓታት የተከናወኑ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴዎችን በመገምገም ለታለመው ግብ ስኬት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀመጠዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በግምገማው ግብረ ሀይሉ የአጭር እና የረጅመ ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት በፍጥነት ወደ ስራ መግባቱን አድንቀው፤ በነበረው የ72 ሰዓት ጊዜ ውስጥ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆኑን ገልፀዋል።

አክለው ሆስፒታሉ ባጭር ጊዜ የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችል በተሰራው ስራ አገልግሎቱን እንዲጀምር ማድረግ መቻሉ ትልቅ ዕምርታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ለሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ እና ተቋማዊ አቅም ማጠናከሪያ የቀረበውን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ ህብረተሰቡ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያሰየው በጎ ትብብርና የሰጠው ቀና ምላሽም የሚያስመሰግን መሆኑን አያይዘው ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ሆስፒታሉ በክልሉ ብቸኛ የኩላልት እጥበት ማዕከል መሆኑን ጨምሮ የተኝቶ ህክምና እንዲሁም  የተለያዩ ወሳኝ የህክምና አገልግሎቶችን ከክልሉ አልፎ ለቀጠናው ህብረተሰብ ጭምር የሚሰጥ አንጋፋ የህክምና ተቋም ከመሆኑ አንጻር፤ ግብረ ሀይሉ ለመልሶ ማቋቋሚያ ሀብት የማሰባሰብ ተግባር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

በዚህ ረገድ ግብረ ሀይሉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች እና የማህብረሰብ መሠረቶች ተሳትፎን ባረጋገጠ መልኩ እና የተለመደ ኢትዮጵያዊ የህብረትና የትብብር እሴታችንን በሚያሳይ አግባብ የተደራጀ ሀብት የማሰባሰብ ስራ መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ሆስፒታሉ የሰው ህይወት ለመታደግ የሚሰራ አንጋፋ ተቋም ከመሆኑ አንፃር፤ የተቋረጡ ህክምናዎች በፍጥነት ተመልሰው የተሻለ አገልግሎቶ መስጠት እንዲችል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርበ ማድረግ እንደሚገባቸውም በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም ግብረ ሀይሉ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በመለየትና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማስተባበር በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ገብቶ መስራት እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ሆስፒታሉን ባጭር ጊዜ በቀደመ የተሟላ ተቋማዊ አቅሙ የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት እንዲችል ለማስቻል ያለሙ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ግምገማውን አጠናቀዋል፡፡

Leave a Reply