
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚንስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በሳውላ ከተማ በክልሉ መንግስት ድጋፍ የተገነባ የንፁሁ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት በይፋ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ እና ክቡር ሚኒስትሩ ለምረቃ መርሃ ግብሩ ጎፋ ዞን፤ ሳውላ ከተማ ሲደርሱ በክልሉና በጎፋ ዞን አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም በጋልማ እና በሳውላ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።






የተመረቀው የንጹህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የተገነባ ፕሮጀክት ሲሆን፤ ከ1 መቶ 35 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ታውቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሳውላ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቱ የከተማዋን ነዋሪዎች የንፁሁ የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡



የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በብድር እና በተዛማች ፈንድ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የተገነባ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የሳውላ ከተማን ከፍ የሚያደርግ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከተማዋን ፅዱና ለነዋሪው ምቹ ለማድረግ በመደረግ ላይ ላለው ጥረት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።



ውሃ ህይወት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጠብቆ ተንከባክቦ በማቆየት ህብረተሰቡን በአግባቡ ማገልገል እንዲችል መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ፍትሃዊ የንፁህ ውሃ ተጠቃሚነትንና ተደራሽነትን ለማስፋት የውሃ ተቋማትን የማስተዳደር አቅምን ማጎልበት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡



በዘላቂነት ውሃ ለማግኝት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ስራዎችን አጠናክሮ ተፈጥሮን መንከባከብ እንደሚገባ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ አረንጓዴ አሻራን ባህል በማድረግ ዛፍ የመትከልና ተፈጥሮን የመጠበቅ ስራዎችን በዘላቂነት እንዲያከናውን ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡



የክልሉ መንግስት መሠረታዊ የሆነውን ፍትሃዊ የንፁህ ውሃ ተጠቃሚነትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፌዴራል መንግስት እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ህብረተሰቡ ጠንካራ የውሃ ተቋም በመገንባት የውሃ ተጠቃሚነትን ለማስፋት የውሃ የክፍያ ታሪፍን በማሻሻል አገልግሎቱን መጠቀም ይገባዋል ብለዋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም ለኢፌድሪ ውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እና ሌሎች ለፕሮጀክቱ ስኬት የድርሻቸውን ላበረከቱ አካላት በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በቡካላቸው፤ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በክልሉ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው የሳውላ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚሁ ጥረትና ትብብር አካል መሆኑን ጠቅሰው ለውሃ ተገቢውን ታሪፍ በመክፈል ውሃው ለረዥም ጊዜ መጠቀም እንዲቻል መስራት አለባችሁ ብለዋል።
በተጨማሪም ርዕሰ መስተዳድሩ እና ክቡር ሚኒስትሩ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አካል በሳውላ ከተማ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።





