የክልሉ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በ27ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 27ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በ27ኛ መደበኛ ስብሰባው፡- የክልሉን መንግስት የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ፣ በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት እና ጠቅላላ ምርት (Regional GDP) ጥናት  በተመለከተ እንዲሁም የተለያዩ ረቂቅ ደንቦችና አዋጆችን መርምሮ ማፅደቅን ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ ውሳኔ በሚሹ ተያያዥ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በክልሉ መንግስት የ2018 የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ሲሆን፤ የክልሉ አስፈጻሚ ተቋማት የስድስት ወር አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ከተያዘው ግብ እና የ100 ቀናት እቅድ አንፃር የተሰሩ ስራዎችን በመለየት ጥንካሬዎችን ማስቀጠልና ክፍተቶችን ለይቶ ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚያስችል ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።  

በውይይቱ በግማሽ ዓመቱ በክልሉ የማስፈፀም አቅምን ከፍ የሚያደርጉና የሚለኩ ቁልፍ ግቦችን በማስቀመጥ እና የፈፃሚ ዝግጅቶችን አድርጎ ወደ ሥራ በመግባት አመርቂ ስራዎች መሰራታቸው ተገምግሟል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ክልላዊና ሀገራዊ የልማትና የብልጽግና ትልሞችን ዕውን ለማድረግ አቅም የሚፈጥሩ ዘርፈ ብዙ የሰላምና ፀጥታ፤ የልማት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ስራዎች መሰራታቸው ተመልክቷል፡፡

በተለይ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረግ ሽግግርን የማፅናት፤ በዋና ዋና የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የትኩረት ዘርፎች፤ በሰው ተኮር ተግባራት እንዲሁም በመደበኛና በንቅናቄ በሚመሩ ሌሎችም የልማት መስኮች አበረታች ውጤት መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡ 

ምክር ቤቱ በውይይቱ በበጀት ዓመቱ በመዋቅሮች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለማጥበብ የታችኛው መዋቅርን የመደገፍ እና የመከታተል ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጿል። 

መስተዳድር ምክር ቤቱ በቀጣይም:- በሁሉም ዘርፎች በ100 ቀናት የታቀዱ ስራዎችን በቀሪ ጊዜያት የማጠናቀቅ፣ ቀሪ የስነ-አካለዊና ቀጣይ የስነ-ህይወታዊ ስራዎች፤ የበልግ አዝመራና የሌማት ቱሩፋት ተግባራት፣ የከተማ ልማትና የገጠር ሽግግር፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የገቢ አሰባሰብ፤ የትምህርትና የጤናው ዘርፍ ስራዎችን እና ሌሎች ተግባራትን የማጠናከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። 

መስተዳድር ምክር ቤቱ በሁለተኛ አጀንዳው የተወያየው በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሁም ጠቅላላ ምርት ጥናት (Regional GDP) በተመለከተ ሲሆን፤ ክልላዊ የመንገድ ኔትወርክ እና Regional GDP የተመለከተ የጥናት ውጤት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓበታል። 

በውይይቱ ጥናቱ የክልሉ መንግስት አዲስ መንገድ ለመስራትም ሆነ ነባሩን ለመጠገን የመንገድ ኔትወርክ በመረጃ ተደግፎ፣ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተጠንቶ መቅረቡ አበረታች መሆኑ ተመልክቷል። ምክር ቤቱ በተጨማሪም የ Regional GDP ጥናቱ ያለንን ፀጋ በአግባቡ በመለየት መጠቀም የሚያስችል መሆኑን በመግለፅ ቀጣይ መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አቅጣጫ አስቀምጧል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል በዝርዝር የተወያየው በቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች እና አዋጆች ላይ ሲሆን፡-

*የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣

*የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተሞች የሆቴል ይዞታ ክፍያ አወሳሰንና አሰባሰብ ሥርዓት ለመወሰን የወጣ ደንብ፣

*የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ደንብ፣

*የገጠር መጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን ማህበር የማህበራት ፌዴሬሽንና የብዝኃ ቀበሌ ማቋቋሚያ ደንብ፤

*የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣንን ለማቋቋም የወጣ ደንብ፣

*የግብርና ትራንስፍርሜሽን ምክር ቤት ለማቋቋም የወጣ ደንብ፤

እንዲሁም የ2018 የግብር ዓመት የደረጃ ለ (ሐ) ግብር ከፋዮችን የመደበኛ ቁርጥ ግብር ለማስከፈል የሚያስችል የገቢ መጠን የወሳኔ ሀሳብ ቀርቧል።

ምክር ቤቱ በቀረቡ 5 ረቂቅ ደንቦች፤ 1 አዋጅ እና 1 የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በህግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ደንቦችን ከነማሻሻያቸው ያፀደቀ ሲሆን፤  አዋጁን መርምሮ ለምክር ቤት መርቷል።

በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።

Leave a Reply