የክልሉ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን የተሰሩ ስራዎች በተመለከተ አጀንዳው ላይ ሲሆን፤ በዚህም በክልሉ በተለያየ ጊዜ በወላይታ፣ ጌዴኦ፣ ጋሞ እና ደቡብ ኦሞ  ዞኖች በተከሰቱ ድንገተኛ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በዘላቂነት ለማቋቋም የተከናነወኑ ስራዎችን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡    

ምክር ቤቱ በውይይቱ በተጠቀሱ ዞኖች በተከሰቱ ድንገተኛ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከዞን አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በርካታ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገምግሟል፡፡

በተለይ በክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ቤቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን የተመለከተው ምክር ቤቱ፤ አስፈላጊ የውሃ፤ የጤና ተቋማትና የትምህርት ቤት መሠረተ ልማቶችን በሟማላት ባጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ መልሶ የማቋቋም ስራውን ለማጠናቀቅ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ምክር ቤቱ በሁለተኛ አጀንዳው በወቅታዊው የማርበርግ በሽታ የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራት ዙሪያ የተወያየ ሲሆን፤ በጅንካ የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ስርጭትን ለመግታት እንዲሁም ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከተል ለመቆጣጠር በመከናወን ላይ ያሉ ስራዎች ያሉበት ደረጃን በመመልከተ በጥልቀት  መክሯል።

በውይይቱ በጅንካ ከተማ የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት በመከናወን ላይ ያለው የተቀናጀ የመከላለከላና የመቆጣጠር ስራ በተደራጀ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

በተለይ የክልሉን የፈጣን ምላሽ መስጫ ማዕከልን ጨምሮ የህክምና ተቋማትን አቅም በማጠናከር  እንዲሁም ከፍተኛ አቅም ያለው ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ እና የኩላሊት እጥበት ማዕከል በጂንካ ሆስፒታል በማቋቋም የተቀናጀ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ እንዲሁም ህክምና በመሰጠት ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ምክር ቤቱ በቀጣይም ከፌዴራል ተቋማት ጋር የተጀመሩ የተቀናጁ ተግባራትን በማጠናከር በሽታውን የመከላከልና ስርጭቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል የበጀት ድጋፍን በተመለከተ አንጀንዳው ላይ የተወያየ ሲሆን፤ የማርበርግ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራትን ለማጠናከር፣ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም  እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች እንዲሁም የፀጥታ ሀይሉን ለማጠናከር ለፖሊስ አባላት ስልጠና የበጀት ድጋፍ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በተጨማሪም ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን አጠናቋል።

Leave a Reply