ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን የነበራቸውን ቆይታ ተከትሎ መልዕክት አስተላልፈዋል

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በጉብኝታቸው በክልሉ በወላይታ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የወላይታ ዞን ቆይታቸው የወላይታ ሶዶ ከተማን የኮሪደር ልማት፤ በዞኑ በአረካ ከተማ አቅራቢያ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘውን የሶማሞ አየር ማረፍያን፤ በዳሞታ ተራራ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡  

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወላይታ ዞን የነበራቸውን ቆይታ ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው መልዕክት  ያስተላለፉ ሲሆን፤ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

“ወላይታ ሶዶ አረንጓዴ ኢትዮጵያን የመገንባት ጽኑ አቋማችን ምስክር ናት። ከአርባምንጭ እስከ ወላይታ ስንጓዝ የአረንጓዴ ልማት ሥራችን ውጤት እንዲሁም አስደናቂ የፍራፍሬ እርሻ ልማት መስክ ተመልክተናል። እነዚህ ጥረቶች የመልከዓ ምድሩን ልምላሜ ከመመለስ ባሻገር የአኗኗር ዘይቤንም የማሸጋገር ሥራዎች ናቸው። በጠንካራ የሥራ ባሕሉ እና ኅብረቱ የሚታወቀው የወላይታ ሕዝብ በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ጠንካራ ሚና መወጣቱን ቀጥሏል።”

Leave a Reply