በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ለክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ባቀረቡት የክልሉ መንግስት የ2018 አጠቃላይ ስራ አፈጻጸም ሪፖርት፡- በክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ካለው እምቅ አቅም አንጻር የክልሉ መንግስት ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመትም በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር፤ ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት በመስራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡  

በዚህ ረገድ፤ በበጀት ዓመቱ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በማስፋፋት ከ57 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እና ከ13 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ክልሉን እንዲጎበኙ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ በዚህም በአጠቃላይ ከ680 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱም ታውቃል፡፡

 ከቅርስ ጥበቃ አንፃርም የሚዳሰሱና የማይዳሰስ ቅርሶች የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ፤ ለትውልድ እንዲተላለፉ፤ ለጥናትና ምርምር እንዲያገለግሉና በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገቡ የማጥናትና መረጃዎችን የማደራጀት፤ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ በስፋት በማከናወን ውጤት መገኘቱንም ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም ቱሪዝምን ዋነኛ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ማድረግ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን በመሙላት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማስፋት፣ ነባሮቹን ደግሞ ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግና የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

Leave a Reply