በ2018 በጀት ዓመት የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የፈጠራቸው ዕድሉችን በመጠቀም በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕድገት ዘርፎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ሪፖርታቸው በተለይ በኢኮኖሚ የዕድገት ዘርፎች በግብርና፤ በንግድና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ፤ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በማዕድን ልማት ዘርፎች የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት በስፋት ዳስሰዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በሁሉም ዘርፍ ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይም የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተረጋጋና ቀጣይነት ያለዉ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የፈጠራቸው ዕድሎችን ተጠቅሞ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በትኩረት ከዳሰሷቸው የኢኮኖሚ ዕድገት ዘርፎች አንዱ የግብርና ልማት ዘርፍ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡

በዘርፉ ባለፉ ጊዜያት በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ የተፈጠረውን መነቃቃትና የተገኘውን ልምድ ይበልጥ በማዳበር በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለሚያረጋግጡ፤ በገበያ ተፈላጊ ለሆኑና ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለሚውሉ እንዲሁም ለኤክስፖርት ምርቶች ምርታማነት ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ በ2017/18 የመኽር ወቅት፤ በልዩ ትኩረት በተሰሩ ስራዎች፤ ከ859 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት በዓመታዊና ቋሚ ሰብሎች በማልማት ከ69 ሚሊዮን ኩ/ል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ፤ ከዕቅድ በላይ 74 ምሊዮን 115 ሺህ 6 መቶ 38 ኩ/ል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።  

በመኽር የተመዘገበውን ምርታማነት፤ በ2018/19 በበልግ ለመድገም በማቀድ፤ ከ8 መቶ 88 ሺህ ሄ/ር በላይ ማሳ በአዝርዕት፣ በሆልቲካልቸር እና በአመታዊ ሰብሎች በማልማት ከ64 ሚሊዮን ኩ/ል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ፤ እስካሁን ከ 496,603 ሄ/ር ማሳ ላይ 24,160,555 ኩ/ል ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በበልግ የምርት ወቅት ባጋጠመ የበልግ ዝናብ መቆራረጥና የስርጭት ሽፋን ማነስ ምክንያት 57,317 ሄ/ር ማሳ ሙሉ በሙሉ ምርት ሳይሰጥ መቅረቱ በበጀት ዓመቱ ያጋጠመ ተግዳሮት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግብርናን በማዘመን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ለመስኖ ልማትና ለሜካናይዜሽን እርሻ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም አርሶ አደሩ ያለን የውሃ ሀብት ተጠቅሞ በአመት ሦሥቴ እንዲያመርት ለማስቻል በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱንም ገልፀዋል፡፡

በዚህ ረገድ በ2018 የመስኖ ልማት፤ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በአንደኛ ዙር መስኖ ልማት ብቻ ከ147 ሺህ ሄ/ር በላይ በማልማት ከ36 ምሊዮን ኩ/ል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ ከእቅድ በላይ በተሰራ ስራ ከ 40 ምሊዮን ኩ/ል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በኩታ ገጠም መስኖ ልማት በአርሶ አደሮች 23 ሺህ 254 ሄ/ር ማሳ በዘር በመሸፈን ከ7 ምልዮን 911 ሺህ ኩ/ል በላይ ከመመረቱም ባለፈ፤ በግል ባለሀብቶች ከ53 ሺህ ሄ/ር በላይ በማልማት ከ7 ምልዮን 673 ሺህ ኩ/ል በላይ ምርት በመስኖ (በአጠቃላይ ከ15 ምልዮን ኩ/ል በላይ) በማምረት ውጤታማ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በበጀት አመቱ ለማዳበሪያና ዘር አቅርቦት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እንዲሁም የአርሶ አደሩን የግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሻሻል እና የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡

ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያግዙ ግብዓቶች በተለይ የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦትና አጠቀቀምን ለማሻሻል በትኩረት በመስራት አበረታች ውጤት መመዝገቡም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ከቡና ልማት ጋር በተያያዘም ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ስራዎች ውጤት መገኙቱን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በ2017/18 የምርት ዘመን ምርት ከሚሰጥ 164,385 ሄ/ር ማሣ፤ 105,260 ቶን ማምረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከቡና ግብይት ስራ አፈጻጸም አንጻርም፤ 13,709 ቶን የታጠበ እና 14,291 ቶን ያልታጠበ በድምሩ 28,0008 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ አመርቂ ውጤት መመዝገቡም በሪፖርቱ ተመልክቷል።  

ከቅመማ ቅመም ሰብሎች ልማት ጋር በተያያዘም በዓመታዊና ቋሚ፤ 88,917.6 ሄ/ር መሬት በማልማት፤ ቋሚ ምርት ከሚሰጥ 63,114 ሄ/ር ማሣ ላይ ከዕቅድ በላይ 5,88,561.1 ኩ/ል በመሰብሰብ 105,512 ቶን ለገበያ ማቅረብ መቻሉም ተገልጿል።

በክልሉ ለእንስሳት ሀብት ልማት ትኩረት በመስጠት በተለይ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፤ ገበያ ለማረጋጋትና ዜጎችን በስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችል አግባብ በትኩረት በመተግበር ተጨባጭ ውጤት መገኘቱም ተመላክቷል፡፡

ለአብነት የዶሮ ልማትን ከማስፋፋት አንጻር፤ በበጀት ዓመቱ 4,054,956 የ1ቀን ዕድሜ ጫጩቶችን ለተጠቃሚ ህብረተሰብ ማሰራጨት ከመቻሉም በላይ 454,732,802 የእንቁላል ምርት መሰብሰብ መቻሉ ታውቋል።

በንብ ማነብ የማር ምርት በተመሳሳይ፤ የማር ምርትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ቴክኖሎጅዎችን በማሰራጨት 17,575 ቶን ማር እና 1,757 ቶን የሰም ምርት ማምረት መቻሉ ተመልክቷል።

በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት ስራዎች፤ በክልሉ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች በራስ አቅም ምላሽ ከመስጠት እንዲሁም በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ከማቋቋም አንጻር በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱም በሪፖርቱ  ተዳሷል፡፡

በሌላ በኩል ክልሉ ካለው ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት አቅም አንጻር፤ በበጀት ዓመቱ የክልሉን አማራጭ የኢንቨስትመንት ዕድሎችና ምቹ ሁኔታዎች በማስተዋወቅ በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ለማላቅ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለተለያየ የኢንቨስትመንት ግልጋሎት የሚውል ከ20 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት በማዘጋጀት፤ ከ 10 ሺህ 646 ሄ/ር በላይ መሬት በገጠርና በከተማ በተለያየ ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚ ባለሀብቶች መተላለፉንም ገልፀዋል፡፡

በተያያዘ የክልሉን ኢንቨስትመንት ከማሳደግ አንጻር፤ የሀገሪቱንና የክልሉን የኢኮኖሚ ዕድገት በመደገፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚሰሩ 208 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች – በግብርና (98)፣ በኢንዱስትሪ (49) እና በአገልግሎት (61) ፍቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በ1 ሺህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በተደረግ ክትትልም- 326 ሙሉ ለሙሉ ወደ ማምረት፣ 314 በከፊል ወደ ማምረት፣ 103 በትግበራ፣ 214 በቅድመ ትግበራ እንዲሁም 36 ወደ ሥራ ያልገቡ ፕሮጀክቶችን በመለየት በስራ ላይ ያሉትን የማበረታታት እና ወደ ስራ ባልገቡት ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን ገልፀዋል፡፡

በገቡት ዉል መሰረት ባላለሙ ኢንቨስተሮች ላይ የእርምት እርምጃ በመወሰዱ ረገድ፤ 85 የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 26 መሬት መቀነስ እና 24 ፈቃድና ውል የመሰረዝ እርምጃዎች በመውሰድ 16,251.2 ሄ/ር መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ መደረጉም ተመላክቷል።

ከማዕድን ሀብት ልማት አንጻርም፤ በበጀት ዓመቱ የክልሉን አቅም በስፋት በማጥናት የመግለጥ እና በዘርፉ የምርት ተጠቃሚነትን የማሳደግ ውጤታማ ተግባራት የተከናወኑ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ 193 ካ.ኪ.ሜ ቦታ የሚሸፍን የቅድመ ዳሰሳ ጥናት የተደረገ ሲሆን፤ በማዕድን ማምረት፤ በጌጣጌጥ ማዕድን አዘዋዋሪነት፤ በከፍተኛና በአነስተኛ ማዕድን ማምረት፤ በማዕድን ምርመራና ፍለጋ እንዲሁም በነዳጅ ተቋማት ብቃት ዕድሳት 755 የተለያዩ ፈቃዶችን መስጠት መቻሉን ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ 20.09 ቶን የጌጣጌጥ ማዕድን ኤክስፖርት መደረጉን እንዲሁም 440 ሺህ ቶን ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና 3.98 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ማዕድን ለኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረት መቻሉም ተጠቁሟል።

ከአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ጋር በተያያዘም በዘርፉ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተፈጠረን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ፈጣንና ጥራት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት የማረጋገጥ ግብ በመጣል ለስኬቱ በበጀት ዓመቱ በትኩረት መሰራቱ ተመልክቷል፡፡ 

በተለይ ነባር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ምርታማነት በማጠናከርና ችግሮቻቸዉን በመፍታት በዘርፉ ለዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር መቻሉንም ተገልጿል፡፡ 

በንግዱ ዘርፍ የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን የበየነ መረብ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ተዘርግተው፤ የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ከመቻሉም በላይ ፍትሃዊ የግብይት ስርዓትን ለማስፈን ትኩረት ተደርጎ በመስራት ውጤት መገኘቱም ተመልክቷል።

ፍትሃዊ የግብይት ስርዓትን በማስፈኑ ረገድ፤ ህግን በተፃረረ መልኩ በንግድ ዕቃዎች ላይ ግብይት በፈፅሙ የንግድ ድርጅቶች ላይ የእርምት እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተያዙ ንብረቶችም ተወርሰው ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን መደረጉም ተገልጿል።

Leave a Reply