
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በ1ኛ ዙር ያሰለጠናቸው 662 ምልምል ኮንስታብል ፖሊሶች በምዕራብ አባያ ጊዜያዊ ፖሊስ ማስለጠኛ አስመርቋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ባስተላለፉት መልዕክት በክልላችን ታሪክ የመጀመሪያ ፖሊስ አባላትን በማስመርቅ ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የጀመርነውን ጥረት ማጠናከር ችለናል ብለዋል።



ለክልላዊ የሰላም ተምሳሌት ራዕይ ስኬት የፀጥታ መዋቅሩን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህን ለማሳካት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች በመስራት ባጭር ጊዜ ብቃት ያለው የፖሊስ ኃይል ማፍራት በመቻሉ መደሰታቸውን ገልፀዋል።
የፖሊስነት ሞያ እጅግ የተከበረ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሰላማችን በእጃችን እንዲሆን ለሞያው እና ለራሱ ተገዢ የሆነ ፖሊስ ሁልጊዜም ተፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።



በክልሉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለስምሪት ብቁ የሆኑ የፖሊስ አባላት መመረቃቸው የተቋም ሪፍርም ስራዎቻችን ፍሬ በማፍራት ላይ መሆኑን በተግባር የሚያሳይ ነው ሲሉም አክለዋል።
ፖሊስነት የህብረትና የአንድነት ሳይንስ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በተናጠል ሳይሆን በጋራ ሲከድ ሁሌም አሸናፊ መሆን ስለሚቻል ተመራቂዎች ህዝቡን በሰባዓዊነት በአንድነት መንፈስ ለማገልገል መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።


ለሰው ልጅ ራሱን ሰጥቶ በጀግንንት ህዝብን የሚያገለግል ፖሊስ መሆኑንም ገልፀው፥ ከሌሎች ተመርጠው ሰልጠነው ለምረቃ ለበቁ ሰልጣኞች፣ ለአሰልጣኞች እና በስልጠናው ወቅት ድጋፍ ላደረጉ ለደቡብ እዝ ስልጠና ማዕከል ምስጋና አቅርበዋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ ህግን በአግባቡ በማስከበር የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ህዝቡን ባለቤት የሚያደርግ፣በአዓምሮው የበሰለ፣ በስነ-ምግባር የታነፀ የፖሊስ ሃይል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የክልሉ ፖሊስ ለህዝብና ለህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ የቆመ፣ መሰረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የሚያከብርና የሚያስከብር፣ የዜጎችን ህይወትና ንብረት ለመጠበቅ ቁርጠኛ የሆነና ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳ መሆኑን ተናግረዋል።


የፖሊስ ሀይል የዘጎችን ሰላም ከመጠበቅ አልፎም የክልሉን ልማት እና ዕድገት ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና ያለው ወሳኝ የልማት ሃይል መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል።
ተመራቂዎቹ ሙያው በምጠይቀው ልክ ብቁ ሆነው ቀጣይ በሚሰማሩበት ፖሊሳዊ ሃላፊነት ህብረተሰቡን በቅንነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው አሳስበዋል።



በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ተመራቂ ምልምል ኮንስታብል ፖሊሶቹ፤ በስልጠናው የቀሰሙትን የተለያዩ የተኩስና የውጊያ ትርዕቶች፤ አካባቢን ከጠላት መከላከልና ወደ ጠላት ምሽግ በመግባት ምርኮ መማረክን ጨምሮ የተለያዩ ትርዕቶችን አሳይተዋል።




ከትርዕቶቹ መካከል የመኝታ፣የእንብርክክና የቁም የተኩስ ትርዕቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ ጥይት ሳይባክንና ዓላማቸውን ሳይስቱ ጠላትን እንዴት መመከት እንደሚቻልና የአካባቢን ሰላም መጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስነ-ዘዴዎችን በተግባር አሳይተዋል።
የክልሉ መንግስት ሕግና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በመጠበቅ እና የሕግ የበላይነትን በማስፈን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለማጽናት ህዝቡን ባለቤት ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ጨምሮ የክልሉን የፀጥታ ተቋማት ተቋማዊ አቅም የሚያጎለብቱ ተከታታይ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡



የዚሁ አካል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የፖሊስ ተቋማትን የህብረተሰቡን ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት መፈጸም በሚችሉ፤ በሙያዊ ስነ-ምግባር በታነጹና ብቁ በሆኑ የፀጥታ ሀይል ለማጠናከር በመጀመሪያ ዙሩ ያሰለጠናቸውን 662 ምልምል ኮንስታብል ፖሊሶች አስመርቋል፡፡



በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ክቡር መስተዳድሩ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት እና የዕውቅና ሰርቴፍኬት አበርክተዋል።




