ለኦቶና ሪፈራል ሆስፒታል መልሶ ግንባታና ተቋማዊ አቅም ማጠናከሪያ ሀብት ማሰባሰብ በይፋ ተጀመሯል

ለኦቶና ሪፈራል ሆስፒታል መልሶ ግንባታ እና ተቋማዊ አቅም ማጠናከሪያ የሚውል ሀብት የማሰባሰብ ተግባር በይፋ የተጀመረ ሲሆን፤ ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክትም ጥሪ ቀርቧል፡፡  

በክልላችን በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚገኘው አንጋፋው የኦቶና ሪፈራል ሆስፒታል ሐምሌ 19/2017 ዓ/ም የደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ በሆስፒታሉ ላይ ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት ማድረሱ ይታወቃል፡፡

የክልሉ መንግስት ሆስፒታሉ ባጭር ጊዜ በቀደመ የተሟላ ተቋማዊ አቅሙ የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት እንዲችል ለማስቻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል።

ለዚህም ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ ሀይል በማቋቋም የስራ ስምሪት የሰጡ ሲሆን፤ ግብረ ሀይሉ በፍጥነት ወደ ስራ በመግባት የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ሆስፒታሉ በክልሉ ብቸኛ የኩላልት እጥበት እና ህክምናን ጨምሮ የተለያዩ ወሳኝ የህክምና አገልግሎቶችን ከክልሉ አልፎ ለቀጠናው ህብረተሰብ ጭምር በመስጠት እጅግ በጣም ከፍተኛ አስትዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኝ አንጋፋ የህክምና ተቋም ከመሆኑ አንጻር፡-

የሆስፒታሉ መልሶ ጥገና እና ተቋማዊ አቅም ማጠናከሪያ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍና የጋራ ርብርብ የሚፈልግ መሆኑ ተመልቷክል፡፡

በመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ግብረ ሀይሉ የክልሉን ህዝብ የተለመደ ኅብረትና ትብብር ባረጋገጠ መልኩ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት እሴታችንን በተጨባጭ በሚያሳይ አግባብ ለሆስፒታሉ መልሶ ጥገና የሚውል ሀብት የማሰባሰብ ስራ በይፋ ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ለሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ እና ተቋማዊ አቅም ማጠናከሪያ የመቶ ሚሊዮን ብር ድገፍ የሚያደርግ መሆኑን በመግለጽ ፈር የቀዳዱ ሲሆን፤ በክልሉ የሚገኙ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮችም የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቀረበውን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎም በክልሉ የጋሞ ዞን አስተዳደር ፈጣን ምላሽ በመስጠት 1 ሚሊየን 5 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የ 1 ሚሊየን ብር ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡

የጎፋ ዞን አስተዳደር በተመሳሳይ የመጀመሪያ ዙር ከ6 መቶ ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ ሆስፒታሉ በመሉ ተቋማዊ አቅሙ የተለመደ አገልግሎቱን መስጠት እስክችል ድጋፉ የሚቀጥል መሆኑን ገልጿል፡፡

ከግሉ ዘርፍ የአቶ አንጅሎ አርሾ ቤተሰቦች በጋራ የ750 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ ሌሎች ባለሀብቶችና የግሉ ዘርፍ ተቋማትም ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሆስፒታሉ ከሚሰጠው ከፍተኛ ግልጋሎት አንጻር ሁሉም ባለድርሻ አካላት፤ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፤ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ አቅሙ በፈቀደ መልኩ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዲችል የሆስፒታሉ አስተዳደር ይፋዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ አካውንት ከፍቷል፡፡

በመሆኑም የሆስፒታሉ አስተዳደር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፈተው አካውንት በመጠቀም ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን እንዲያሳይ ጥሪ ቀርቧል፡-

*በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፡- 1000709948737 (yeotona referal hospital m/maderaja)

ስንተባበር እንችላለን!!!

Leave a Reply