ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጌዴኦ ዞን የደረሰውን አደጋ ተከትሎ የክልሉን የአደጋ ስጋት ምክር ቤት በመሰብሰብ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል 

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጌዴኦ ዞን ባደረጉት የስራ ቆይታ በዞኑ በራጴ ወረዳ የተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ ያደረሰውን ጉዳት በመመልከት በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በስፍራው ተገኝተው ያፅናኑ ሲሆን፤ የክልሉን የአደጋ ስጋት ምክር ቤት በመሰብሰብም በቀጣይ ተግባራት ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በምክክሩ በዞኑ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋው በደረሰባቸው አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ ያስከተለው ጉዳት እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ገልፀው፤ በህይወት የተረፉ ወገኖችን ለመታደግና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ክልላዊና ዞናዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል።  

የሰው ልጆ ህይወቱን ማትረፍ በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ ህይወቱ ሲያልፍ ማየት እጅግ ልብ ሰባሪ ክስተት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለአደጋው ምላሽ በመስጠቱ ረገድ ከአጭር ጊዜ እና ከረጅም ጊዜ አኳያ መሰራት ያላበቸው ስራዎችን በፍጥነት ለይቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከአጭር ጊዜ አንጻር በተለይ ለተጎጂዎች አስፈላጊ የሆኑ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፎችን ከማድረግ ጀምሮ በጊዚያዊ መጠለያ ያሉ ዜጎች አስፈላጊ መሰረታዊ ነገሮች እየተሟላላቸው ጤናቸው የተጠበቀ እንዲሆን እንዲሁም ለሌሎች ቀውሶች ሳይጋለጡ  ይህን ፈታኝ ወቅት ማሻጋር  የሚያስችሉ አፋጣኝ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

በአካባቢው በቀጣይም ከፍተኛ ዝናብ የሚዘንብበት አዝማሚያ በመኖሩም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ስፍራዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ደህንነቱ ወደ ተረጋገጠ ቦታ በማሻገር ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡ 

ከረጅም ጊዜ አኳያም በአካባቢው ለመሬት ናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት እና በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባባበር ችግሩን በዘለቄታዊነት ለመፍታት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

የጌዴኦ ማህበረሰብ በክልላችን ከተፈጥሮ ጋር ባላቸው የተለየ ጥብቅ ቁርኝት ብሎም በደን አጠባብቅና በጥምር ግንብርና ከሚታወቁ ማህበረሰቦች ግንባር ቀደም መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የደረሰው አደጋ በአካባቢው ይደርሳል ተብሎ ያልተገመተ በመሆኑ በቀጣይ በተፈጥሮ ጥበቃ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለየቶ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጋር ተያይዞ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም መሰል አደጋዎች የተከሰቱና በቀጣይም ሊከሰቱ የሚችሉ በመሆኑ፤ ለናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የአደጋ ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች በየደረጃው ያለው አመራር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሲከናወኑ የቆዩ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ወቅቱ ከመቸውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ የመጠያየቅና የመደጋገፍ ባህል እሴቶቻችንን ይዘን በትብብርና በአንድነት የሚንቆምበት በመሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብ የተጎዱ ወገኖቻችንን በማፅናናት እና በመደገፍ  ከጎኑ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የአስቸካይ የሰብዓዊ ድጋፎች ከማቅረብ ባለፈ ችግሩን በዘለቀታዊነት መፍታት የሚያስችሉ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ምክክሩን አጠቃለዋል፡፡

Leave a Reply