
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል፤ የኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን ብዝኃነት በማክበር፤ የሕዝቦች ትስስርን በማጠናከር፤ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቶችን በማጎልበት ለእኩልነት፤ ለፍትሐዊነት፤ ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ለፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ አውድ በመፍጠር ለፌዴራል ሥራዓታችን መጎልበትም ሆነ ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር የላቀ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
ክብረ በዓሉ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፌዴራሊዝምን እሴቶች ተላብሰው፤ ለሀገራዊ ልዕልና አምድ በሆኑ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩበት፤ ለጋራ ዘላቂ ሰላምና ልማት ትብብራቸውን የሚያጠናክሩበት፤ ከፋፋይ ነጠላ ትርክቶችን በማክሰም፤ በገዥ የወል ትርክቶች ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን የሚያፀኑበት በመሆኑም ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
በበርካታ አኩሪ ድሎች የኢትዮጵያን የንጋት ዘመን ጅማሮ በማብሰር ወደ ስራ በገባንበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የሚከበረው የዘንድሮ በዓል፤ ዘመን በተሻገረ አብሮነት በብዝኃነት ውስጥ ያበበው የሕዝቦች አንድነት የህልውናችን መሠረት መሆኑን ከትላንት የጋራ ታሪካችን ተገንዝበን ቃልኪዳናችንን በማደስ፤ ለቀጣይ የብልጽግና ጉዟችን ቁልፍ የሆነው ህጋዊና ታሪካዊ የባህር በር ባለቤትነታችንን ለማረጋገጥ ለአንድ ዓላማ በጋራ የመቆም ትዕምነትን ተላብሰን ለብሔራዊ ጥቅማችን በጋራ የምንቆምበት ሊሆን ይገባል፡፡
ልዩነታችን ውበት፤ ብዝኃነታችን ፀጋ፤ አንድነታችን ኃይልና የስኬታችን መሠረት ነው!!
እንኳን ለ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አደረሳችሁ!!
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ




