
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሕዝብ ምክር ቤትና የብሔረሰቦች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በተገኙበት ወቅት፤ የሁለቱን ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራ መጀመር በማብሰር የክልሉን መንግስት የ2018 የትኩረት አቅጣጫዎች ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ መዳረሻውን ዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ያደረገው ክልሉ፤ ባለፈው የ2017 በጀት አመት በሰላምና በልማት አርበኛወ የክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎና ተደማሪ አቅም በሁሉም የልማት አውታሮች አመርቂ ስኬቶች በማስመዝገብ ውጤታማ ጉዞ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በተያዘው የ2018 በጀት አመትም በሁሉም የሰላም፤ የልማት እና የመልካም አስተዳደር መስኮች የተመዘገቡ አስደናቂ ውጤቶችን በማላቅ እና በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ገልጦ በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የክልሉን ህዝብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡
በዋና ዋና የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ በማተኮር በዳሰሱት የ2018 የልማት ዕቅድም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረግ ሽግግርን የሚያፀኑ እና ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የብልጽግና ግብ ስኬት አቅም የሚፈጥሩ ዝርዝር የትኩረት አቅጣጫዎችን ማመላከታቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ካስቀመጡት የክልሉ መንግስት ዋና ዋና የ2018 የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል፡-
*ሰላምና ፀጥታ፡- የልማት መሠረት የሆነውን ሰላም የክልሉ መለያና አርማ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ የክልሉን አንጻራዊ ሰላም ለማፅናት በልዩ ትኩረት ይሰራል፤
*የህዝቦች አንድነትና ትብብር፡- የክልሉን ህዝቦች አንድነት ማፅናትና ኅብረትና ትብብር ማጎልበት የክልሉ መንግስት የሰላምና የልማት አጀንዳ ማዕከል፤ የህዝቦችን አብሮ የማደግና የመልማት ትልም ማሳኪያ እና በተደማሪ አቅም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጫ መንገድ ማድረጉ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤
*የግብርናው ዘርፍ፡- በኢኮኖሚው ረገድ የክልሉ መንግስት ቀዳሚ ትኩረት በሆነው ግብርና፤ በክልሉ ያሉ የመልማት አቅሞችና ፀጋዎች በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርናን አቅዶ በመተግበር እና የመስኖ አውታሮችን በማስፋት ምርታማነትን 20 በመቶ ለማሳደግ መስራት፤
*የቱሪዝም ዘርፍ፡- ክልሉ በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል፤
*የማዕድን ሀብት ልማት፡- በዘርፉ የክልሉን አቅም በስፋት በማጥናት የመግለጥ፤ ጥናታቸው የተጠናቀቀን ወደ ምርት የማስገባት እንዲሁም በምርት ላይ የሚገኙትን የማምረት አቅም የማስፋት እና በዘርፉ የምርት ተጠቃሚነትን የማሳደግ ተግባራት፤
*የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ፡- በዘርፉ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግና ለተኪ ምርቶች ምርታማነት ትኩረት በመስጠት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ለማሳደግና ጥራት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት ለማረጋገጥ መስራት፤
*በኢንቨስትመንት ዘርፍ፡- ዘርፉን ይበልጥ በማነቃቃትና አልሚ ባለሃብቱን በስፋት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፤ በማዕድን ልማትና በሌሎችም አማራጮች በማሰማራት በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ለማላቅ ይሰራል፤
*የገቢ አሰባሰብ፡- የክልሉን የገቢ ሴክተር ተቋማዊ አቅምን በማጎልበት፤ የገቢ መሰረት በማስፋትና የገቢ አሰባሰብ ተግባርን በልዩ ትኩረት በተቀናጀ አግባብ በመምራት፤ በዘመኑ ከታቀደው በላይ ገቢ በመሰብሰብ የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ መስራት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው፤
*ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ፡- በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ የስራ ዕድሎችን የመፍጠር፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የስራ ዕድሎችን የማስፋት፤ የብድር፥ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን በብዛትና በጥራት በማዘጋጀት እንዲሁም ብቁ ስልጠናዎችን በመስጠት የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል፤
በተጨማሪም በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በትምህርትና ጤና፤ በመንገድና ውሃ መሠረተ ልማት፤ በከተሞች ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ልማት የተጀመሩ ውጤታማ ስራዎችን የማጠናከር፤ አገልግሎት አሳጣጥን የማዘመን ተግባራት የማስፋት እንዲሁም ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሠረት የሆኑ ስራዎችም ተጠቃሽ የትኩረት መስኮች ናቸው፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ በአጠቃላይ በ2018 ለተጣሉ ግቦች ስኬት ነባሩ የስራ ባህል ላይ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣትና አዲስ የአስተሳሰብና የተግባር ብሂልንና የስራ መርህን በመሰነቅ፤ ከመቸውም ጊዜ በላይ ኅብረት ትብብርን አጠናክሮ በጊዜ የለንም ስሜት፤ ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት አግባብ ለላቄ ውጤት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡