
ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው በኢኮኖሚው ረገድ የክልሉ መንግስት ቀዳሚ የትኩረት ዘርፍ ለሆነው ግብርና በ2018 የበጀት ዓመትም ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


በባለፈው የበጀት አመት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ እና ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መገኙቱን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተያዘው የበጀት ዓመት በመጠንም ሆነ በጥራት ምርትና ምርታማነት ማላቅ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡



ለዚህም በክልሉ ያሉ የመልማት አቅሞችና ፀጋዎች በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል፤ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የታገዘ ግብርናን አቅዶ በመተግበር በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን 20 ከመቶ በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡



በበጀት አመቱ ግብርናን በማዘመንና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና አመራረት ስርዓትን በማጎልበት ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅና ያሉ የውሃ አማራጮችን በሙሉ ዐቅም አሟጦ መጠቀም እንዲቻል ለመስኖ ልማትና ለሜካናይዜሽን እርሻ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዚህ ረገድ የመስኖ አቅምን ለማጎልበት በባለፉ ዓመታት የተጀመሩ የመስኖ አውታሮችን ማጠናቀቅና አዳዲስ የመስኖ ግንባታዎችን ጥናትና አቅምን መሰረት ባደረገ መልኩ በመጀመር አርሶ አደሩ ያለን የውሃ ሀብት ተጠቅሞ በአመት ሦሥቴ እንዲያመርት ለማስቻል የሚሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ምርታማነትን ለማሳደግ አዳዲስ አሰራሮችን በማላመዱ ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የኩታ ገጠም እርሻን ለማስፋፋት፤ ገበያን መሰረት ያደረገና የአቅርቦት ችግርን የሚፈታ የአመራረት ዘይቤ ለማጠናከር፣ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሰብል ምርቶች ለማሳደግ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተረጅነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የታሪክ እጥፋት ለማስመዝገብ በሚያስችሉ መስኮች በተለይም በሰብል ልማት፤ በፍራፍሬ እንዲሁም በቡናና ቅመማ ቅመም ዘርፍ የክልሉን እምቅ አቅም በመጠቀም ምርታማነትን በመጠንም በጥራትም ለማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑንም አስምረዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት ስራዎች፤ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የእንስሳት ሀብት ልማት ተግባራት እንዲሁም በክልሉ ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በራስ አቅም ምላሽ ከመስጠት አንጻር የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ርብርብ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡