
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ቁጥጥር የማብሰሪያ እና የምስጋና መርሃ ግብር ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤቨር ማሲንጋን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።



በመርሃ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ በማርበርግ ቫይረስ የታመሙ ወገኖችን እየረዱ ባሉበት ወቅት በበሽታው ተይዘው ሕይወታቸውን ላጡ ሁለት የጤና ባለሙያዎች የመታሰቢያ ሀውልት በጅንካ ሆስፒታል አኑረዋል።



ዶ/ር ጌትነት አቡዬ እና ነርስ አማኑኤል ካሳ ለሕይወታቸው ሳይሰስቱ የማርበርግ ቫይረስን በመዋጋቱ ሂደት ህይወታቸው ማለፉን ምክንያት በማድረግ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ የመታሰቢያ ሀውልት የተቀመጠላቸው መሆኑ ተገልጿል።



ርዕሰ መስተዳድሩ በማብሰሪያ መርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተናበን ተባብረንና ተቀናጅተን በመስራታችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን መቆጣጠር ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።



በመላው ኢትዮጵያዊያን ትብብር እና በጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ብርቱ ትጋት በሽታውን መቆጣጠር መቻሉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለሎችን ከበሽታው ለማዳን የራሳቸውን ህይወት የሰዉ የጤና ባለሙያዎች በታሪክ ሁሌም ከራስ በላይ ለሌሎች የማሰብ ተምሳሌት ተደርጎ የሚታወስ መሆኑንም ገልፀዋል።
የማርበርግ ቫይረስ ስርጭት ውጤታማ የመከላከልና የመቆጣጠር ሂደት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የተገነባን ወረርሽኝን የመከላከል ሀገራዊ ተቋማዊ አቅም በተግባር ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ የበሽውን መከሰት ያመላከቱ የቅኝት መረጃዎች መገኘታቸውን ተከትሎ የክልሉ መንግስት በፍጥነት ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበት ተቀናጅቶ በመስራት ወረርሽኙን መቆጣጠር መቻሉንም አስረድተዋል።
የጤና ሚንስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት ብሎም በየጊዜው ክትትል በማድረግ በሽታውን በመቆጣጠር ሂደት ያደረጉት አስትዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።



ከዚህም በተጨማሪ በሽታውን በመቆጣጠር ሂደት የአጋር ድርጅቶች ሚና የጎላ መሆኑን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ቫይረሱን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር የድርሻቸውን የተወጡ ባለድርሻ አካላትንም አመስግነዋል።
ተቀናጅተንና ተናበን ከሰራን በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ እንችላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ተናቦ በመስራት በሁሉም ዘርፍ ውጤት ማስመዝገብ የሚቻል መሆኑን ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ የተመዘገበው ታላቅ ስኬት ማሳያ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥ የማይታለፍ የሚመስለውን ከባዱን ጊዜ አልፈን፤ ወረርሽኙን በስኬት በመቆጣጠር ለዛሬው ቀን በመድረሳችን እንኳን ደስ ያለን ብለዋል።
የማርቨርግ ቫይረስ በሽታን መቆጣጠር መቻሉ እንደ ሀገር ወረርሽኝን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ የጤና ስርዓት መፈጠሩን አመላካች መሆኑንም ሚንስትሯ ገልፀዋል።
ህዝብ አስተባብረን ከሰራን በአጭር ጊዜ የትኛውንም ስኬት ማስመዝገብ እንችላለን ያሉት ዶ/ር መቅደስ፥ ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር መቻሉ ለዚህ ትምህርት መሆኑን ተናግረዋል።


በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ በሽታ በመቆጣጠሩ ሂደት የክልሉ መንግስት ያሳየውን ቁርጠኝነት ያደነቁት ሚኒስትሯ፤ የተመዘገበው ውጤት በቅንጅት የመስራትንና በሽታን የመከላከል የቅድመ ቅኝት ስራዎች ውጤታማነት የሚያመላክት መሆኑንም አብራርተዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ላይ የቅኝት ስራ መሰራቱን የገለፁት ዶ/ር መቅደስ፥ እንደ ሀገር የማይበገር የጤና ስርዓት ለመዘርጋት በትኩረት በመሰራ ላይ መሆኑን አያይዘው ገልፀዋል።



በመርሃ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከሉ ሂደት ላበረከቱት ከፍተኛ አስትዋፅኦ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።



ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ እና ክብርት ሚኒስትሯ የበሽታውን መከሰት ያመላከቱ መረጃዎች መገኘትን ተከትሎ፤ በሽታውን ለመከላከል እና ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ለሚያስችሉ ተግባራት ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ በሰጡት ጠንካራ የተቀናጀ ስትራቴጂካዊ አመራር በሽታውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉ ተግልጿል፡፡






በተጨማሪም በየደረጃው ያሉ የጤናው ዘርፍ አመራሮች፤ ባለሙያዎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረገው የተቀናጀ ርብርብ ላበረከቱት አስትዋፅኦ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።




