
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት 5ኛው ሀገር አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ ”ኃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለአብሮነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም፤ የመቻቻልና የብዝኃነት ተምሳሌት በሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በሰላም ሰገነቷ አርባ ምንጭ ከተማ በታላቅ ህዝባዊ ተሳትፎ ተካህዷል፡፡


በጉባኤው የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ በህይወት የመኖር መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰላም ሲኖር ሰው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ በሰብአዊ ልዕልናው ልክ ሰርቶ ለሀገር ዋልታና ማገር መሆን የሚያስችለውን ፍሬ በማፍራት አለምን የተሻለ ማድረግ ይቻለዋል ብለዋል፡፡


ለሰላም መረጋገጥ የመቻቻል፤ የመረዳዳትና የመከባበር እሴቶችን ማጎልበት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ በብዝኃነት ውስጥ ያበበ አንድነታችን የህልውናችን መሠረት መሆኑን በውል ተገንዝቦ፤ ከመጠፋፋት ይልቅ ለጋራ ተጠቃሚነት ተባብሮ በጋራ መኖርን ምርጫችን ማድረግ ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡



በዚህ ረገድ ሀይማኖታዊ እሴቶች ቁርሾና በደልን በይቅርታ በማሻገር እንዲሁም ውሸትና ሴራን ነቅሎ ሀቅን፤ ቅንነትንና ደግነትን ባህል በማድረግ ሰላምን ከማንገስ ባለፈ፤ ከተፈጥሮዊ ልዩነቶች ባሻገር በፍቅር በመደመር ወዳለምነው የብልጽግና ማማ እንዲደርስ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡



ሰላም ስለተመኘነው እና ስለዘመርነው ብቻ አይረጋገጥም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሁሉም ለሰላም መረጋገጥ ቁርጠኛ ሆኖ ከልብ በመነጨ ትብብር ብርቱ ጥረት ማድረግን፤ ስለሰላም መከፈል ያለበት ዋጋን መክፈልን ይጠይቃል ብለዋል፡፡



በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሀይማኖታዊ አስተምህሮ ያፈነገጡ፤ ሰላምን በማደፍረስ አላስፈላጊ ዋጋ የሚያስከፍሉና የልማት አቅማችንን የሚሸረሽሩ ድርግቶች የሚስተዋሉ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ይህን አደገኛ ልምምድ የሀይማኖት ተቋማት የህልውና ጉዳይ በማድረግ ትውልዱን በአስተምህሮ ለማነጽ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡


ሰላምን ለማስፈን፤ ለመጠበቅና ለማፅናት የሀይማኖት ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም አስፈላጊው እሴት፤ የዳበረ ዕውቀት፤ አስተምህሮ እና ተቋማዊ አቅም ያላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ተቋማቱ በዚህ ረገድ ሰላምን በማፅናት የመንግስትን ጫና ማቅለል ይገባቸዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ያ ሲሆን መንግስት ሙሉ ትኩረቱንና አቅሙን ልማት ላይ በማዋል በህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ባጠረ ጊዜ ዕውን በማድረግ ሀገርን ማሻገር ያስችለዋል ሲሉ አስምረዋል፡፡



ባለፉ የለውጥ አመታት በብልጽግና ፓርቲ መሪነት፤ በተለይም በክቡር ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ቁርጠኛ አመራር ካንቀላፋንበት ረዥም እንቅልፍ ነቅተን የኢትዮጵያን የንጋት ዘመን አብሳሪ የሆነው ህዳሴን በድል ከማጠናቀቅ ባለፈ የማይቻሉ የሚመስሉ አስደማሚ ስኬቶች በማስመዝገብ አይቀረ የሆነው የሀገራችንን ብልጽግና አሻገሮ ማየት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡



ቀጣይ የመንግስት ትኩረት ሰላምን በማጽናት ለሁለንተናዊ ብልጽግናችን መረጋገጥ ቁልፍ የሆነው ታሪካዊና ህጋዊ የወደብ ባለቤትነታችንን ማረጋገጥ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህ የሀይማኖት ተቋማት ተገቢውን ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ የሀገራችን የማንሰራራት ማሳያ፤ ቀዳሚ የብዝኃ ህዝቦች የጋራ ቤት በሆነው የሰላም፤ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌቱ ክልላችንም፤ ሰላምን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግና በመደመር እሳቤና መንገድ በመመራት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በበርካታ ውጤቶች የታጀበ ስኬታማ ጉዞ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡



ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን በተሸጋገርንበት፤ ተስፋችን ወደ ሚታይና ሚጨበጥ ተለውጦ ወደ ስራ በገባንበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፤ ሰላምን የክልሉ መለያና ዓርማ በማድረግ እና ፀጋዎቻችንን በመግለጥ ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት አግባብ ሌላ ታሪክ ለማስመዝገብ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቄሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የብዝሃ ኃይማኖቶች እና ማንነቶች ባለቤት መሆኗን በመጥቀስ ሁሉም በመቻቻልና በመዋደድ በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር ናት ብለዋል።



በሀገራችን ለሚስተዋለው ሰላም የሀይማኖት አስተምህሮቶች ዋነኛ ድርሻ አላቸው ያሉት ሊቀ ትጉሃን፤ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጋራ ለሀገራዊ ጉዳዮች አፅንኦት ሰጥቶተው እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሀይማኖት ሽፋን የሚደረግ ሴራ ሀጥያት መሆኑን የተናገሩት ሊቀ ትጉሃን ቄሲስ ታደለ፤ ሁሉም ቤተ እምነቶች ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በህዝቦች መካከል ግጭት የሚሰብኩን ሊያወግዙ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በህዝቦች እና በሀይማኖቶች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ የሚሰሩ አንዳንድ ግለሰቦች በመኖራቸው መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያስከበር ጠይቀዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመከባበርና በመቻቻል አብሮ የመኖር እሴቱን እንዲያጠናክርና የብሄርም ሆነ የሐይማኖት ልዩነቶቻችን ጌጦቻችን እንጂ ለችግር መንስኤ ሊሆኑ እንደማይገባም ሊቀ ትጉኃን ቄሲስ ታደለ አስገንዝበዋል።




