ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለ 2018 የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀመጡ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ የ 2017/2018 ክልል አቀፍ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የ 2018 የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ተገኝተው መልዕክት በማስተላለፍ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።  

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይ ባለፉ የለውጥ አመታት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ፍሬ አፍርቶ፤ የብዙሃኑን እምባ ከማበስ ባሻገር በዘርፈ ብዙ በጎ ተግባራት የባህል ዕጥፋት በማስመዝገብ ጭምር ታሪክ በመቀየር ላይ የሚገኝ ውጤታማ ሰው ተኮር ተግባር ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡

አስሮ የያዘን የሃሳብ ድህነት እንጂ የሀብት እጦት አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዘመናት ያለንን ሀብት፤ ዕውቀት፤ ፀጋና ጉልበት የምናይበት የተዛባ ዕይታ በፈጠረው ፈተና፤ ችግሮችን በራስ አቅም ከመፍታት ይልቅ በጠባቂነት መኖራችንን አስረድተዋል፡፡   

ሆኖም ሰው ተኮር የሆነው የለውጡ መንግስት፤ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተግባራትን ባህል አድርጎ በጠንካራ ተቋማዊ ማዕቀፍ በመምራት፤ የጠባቂነት እሳቤን የሰበረ እና በራስ አቅም እንችላለን የሚል እሳቤና አመለካከትን የተከለ የባህል እጥፋት በማስመዝገብ ጭምር አስደናቂ ውጤት ማምጣጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ነባር የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴታችንን የሚያጎለብቱ፤ በርካታ አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን ተጠቃሚ ያደረጉ፤ የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና የልማት ትብብርን ያጠናክሩ እና ለዘላቂ ሰላምና ልማት የጎላ ሚና ያላቸው ውጤታማ ተግባራት በመርሃ ግብሩ መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

የባህል እጥፋት ከሃሳብ ስርፀትና ቁቡልነት ይጀምራል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአንድ ጀንበር በሺህ የሚቆጠሩ የአቅመ ደካማ ቤት ግንባታና እድሳት በራስ ተደማሪ አቅም በማከናወን ጭምር የመጣው ለውጥ የመናበብ፤ የመቀናጀት እና በአንድነት በአንድ ዓላማ የመሰለፍ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎነት ሳይተርፈን የምናከናውነው የተቀደሰ ተግባር ነው፤ በበጎነት የተገኘ ስኬትም ሰብዓዊነት በመሆኑ ከሌሎች ስኬቶች ሁሉ የተለየና የበለጠ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለፈው ጊዜ የተመዘገበው ስኬት ምንም አመርቂ ቢሆን ካለን ፀጋና ፍላጎት አንጻር ገና ብዙ መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ 

ለዚህም ያለን አቅምና ጉልበት በማቀናጀት በክረምት የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋዉም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸው፤ ለተያዘው የ2018 የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡-

በክረምቱ የተሰሩ ስራዎች ቀጣይነትና ቀላቂነት ማረጋገጥ፡- በ2017 የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብርተሰቡን በማስተባበር እና የወጣቱን እንዲሁም የሴቶች ጉልበትና ሀሳብ በማቀናጀት የተከናወኑ በርካታ ተግባራት መልሶ በማየት ለታለመው ውጤት መብቃታቸውን ማረጋገጥ፤ ማጠናከር፤ ማሳደግና ተሞክሮ መቀመር ይገባል፤

ትምህርት ቤቶችን ማዕከል ያደረጉ ተግባራት፡- በሙሉ አቅም ህብረተሰቡን አስተባብሮ ለትምህርት ጥራት መሻሻልና ለተማሪዎች ውጤታማነት ቁልፍ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን በመጻህፍትና ሌሎች ግብዓቶች የማጠናከር፤ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስ የተጀመሩ የማህበረሰብ አቀፍ የት/ት ቤት ምገባን የማጠናከር ተግባራት፤

የወንድማማችነት ትርክትን የመገንባትና የህዝቦች አንድነትን የማፅናት ተግባራት፡- አንዳችን ያለ አንዳችን መቆም የማንችል ስለመሆኑ፤ በብዝኃነት ውስጥ ያበበው አንድነታችንም የህልውናችን መሠረት የመሆኑን እውነታ በውል የሚያስገነዝብ አሻጋሪ የወንድማማችነት ትርክት የማስረጽ፤ እሴት የመትከልና ቤተሰባዊነትን የማጎልበት ተግባራት፤

በተለይ ወጣቶች ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ተግባራትን በማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ትስስሮችንና የልማት ትብብሮችን የማጠናከር፤ ፍቅር፤ ሰላምና አንድነትን በመስበክ ዓርአያ ሆኖ የመገኘት፤ ለክልላችንና ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት ብሎም ለጠንካራ ኅብረ-ብሔራዊ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ጉልህ ድርሻ ማበርከት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ያለንን ጉልበት፤ ዕውቀት እና ሃብት አቀናጅተን በራስ አቅም ችግሮቻችንን ለመፍታት ከተፈጥሯዊ ልዩነቶች ባሻገር ከተባበርን እና በኅብረት ለጋራ ልማት ከተጋን፤ ድህነትንና ኋላቀርነትን ታሪክ በማድረግ ብልጽግናችንን ባጠረ ጊዜ ውስጥ ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉም አያይዘው አስገንዝበዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰብ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም በሁሉም መስክ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በመደረግ ላይ ላለው ጥረት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጋ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአደራ ጭምር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ በክረምቱ የ2017/18 ክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ15 ልዩ ልዩ ተግባራት ከ2 ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ገ/መስቀል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክልሉ መሻገር እንደሚችል የታየበት ቁልፍ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፤ የተገኘው ውጤት አጠቃላይ አመራሩ፣ የወጣቶችና ሴቶች ክንፍ አደረጃጀት እንዲሁም የፓርቲና የመንግስት መዋቅሩ በመደመር ያስመዘገቡት ስራ እንደሆነ ገልጸዋል።     

በ 2017/18 የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ ከ 9 ሺ 200 በላይ ቤቶች መገንባታቸዉንና ከ 6 ሺ 400 በላይ ቤቶች መታደሳቸዉንም አቶ ገ/መስቀል አስታውቀዋል።   

በክልሉ በአንድ ዓመትብቻ ከ 15 ሺህ በላይ ቤቶችን በመገንባትና በማደስ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እምባ ማደስ መቻሉ ብልጽግና ሰዉ ተኮር ፓርቲ ስለመሆኑ የተግባር ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።   

በክልሉ በክረምት ወራት የተከናወነውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋው አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ የክልል አቀፍ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አመራሮች እና መዋቅሮች እውቅና ተሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም ክቡር ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ በ2017 ዓ.ም የክረምት ወቅት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ወጣቶች እውቅና ሰጥተዋል።

እውቅና የተሰጣቸዉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች፤ በክልሉ ያለፈው የክረምት ወቅት በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸው ተገፈልጿል።   

Leave a Reply