ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የጤና ሚንስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጅንካ ሆስፒታል ተገኝተው የማርበርግ ቫይረስ የመከላከልና የክትትል ስራዎች ምልከታ አደረጉ   

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ለጅንካ ሆስፒታል የማልቡርግ ቫይረስን ለማከምና ለሌሎች ህክምናዎች የሚያስፈልጉ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጅንካ ሆስፒታል በመገኘት የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመቆጣጠር በመከናወን ላይ የሚገኙ የክትትል እና ቁጥጥር ስራዎች ምልከታ አድርገዋል።  

ርዕሰ መስተዳድሩ በምልከታው ወቅት በጅንካ ከተማ የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከሰቱን ያመላከቱ መረጃዎች መገኘትን እና በኋላም በላብራቶሪ መረጋገጡን ተከትሎ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በሽታውን የመከላለከላና የመቆጣጠር ስራዎች በተደራጀ መልኩ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል። 

የዛሬው ጉብኝቱ ዋንኛ አላማም ህክምናውን እየሰጠ የሚገኘው የጅንካ ሆስፒታል የተሻለ ህክምና እንዲሰጥ የሚያስችል የተሟላ ቁመና መፍጠር እና ይሄን ስራ እየሰሩ ከሚገኙ አመራሮች እና የህክምና ባለሞያዎች ጋር ለመምከር እንደሆነ ተናግረዋል።

አክለው የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል ለመከላከል የክልሉ መንግስት የፈጣን ምላሽ መስጫ ማዕከል ጅንካ ላይ ተቋቁሞ ከፌደራል ድንገተኛ በሽታ የመከላከልና ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ጋር የተቀናጀ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ በመስጠት ላይ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ማእከላትና የህክምና ተቋማትን የማጠናከር ስራ መከናወኑንም ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በሽታው የተያዘን ሰው የመለየት፣ ቫይረሱ የተገኘባቸውን የህክምና ክትትል የማድረግ እና አዲስ እንዳይከሰት ስርጭቱን የመቆጣጠር ስራ በጠናከረ መልኩ በመካሄድ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ የኢፌዲሪ ጤና ሚንስቴር ከክልሉ መንግሰት ጋር በቅርበት በመስራት ከፍተኛ የመመርመር አቅም ያለዉ ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪም በመላክ ጭምር በሽታውን በላብራቶሪ ከመለየት ጀምሮ አስፈላጊ የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን በመግለጽም በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም አመስግነዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ህብረተሰቡ በሽታው በንክኪ የሚተላለፉ መሆኑን በመገንዘብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዳያደርግ እና ተጋላጭነትን በመቀነስ እራሱን ከበሽታው እንዲከላከልም ጥሪ አቅርበዋል።

በሽታው ከተከሰተ ግዜ ጀምሮ የሰው ህይወት ለማትረፍ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለው በሽታው እንዳይስፋፋ ለሰሩ የጤና ባለሙያዎች፣ የክልሉ የጤና ኃላፊዎች ለዞኑ አስተዳዳሪ እና አመራሮች ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ  በጋራ ተጋግዘን በመስራት  ይሄን ጊዜ እናልፋለን  ሲሉ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።

የኢፌድሪ ጤና ሚንስቴር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው በሽታው እንደተከሰተ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድኖች ቫይረሱ ወደ ተገኘባቸው አካባቢዎች በመላክ የተቀናጀ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል።

የአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ማእከላትና  የህክምና ተቋማትን ማቋቋምና ማጠናከር ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የህክምና አቅርቦቶች እና የህብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫና የቅኝትና ቁጥጥር ስራዎች እየተካሄዱ መሆን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ስለህመሙ ትክክለኛ መረጃ ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲሁም ቫይቨረሱን በተመለከተ ሳይንሳዊ መረጃዎችን እንደ አባሪ በመጠቀም ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ለጅንካ ሆስፒታል የማልቡርግ ቫይረስን ለማከምና ለሌሎች ህክምናዎች የሚያስፈልጉ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የህክምና አቅርቦቶችና የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁሶች ስርጭትም ማድረጉም በጉብኝቱ ተገልጿል።

Leave a Reply